ሰሜን ኮሪያ በፑንግዬ-ሪ የሚገኘውን የኒዩክሌር ሙከራ ጣቢያዋን አፈራረሰች

78
ግንቦት16/2010 ሰሜን ኮሪያ በፑንግዬ-ሪ የሚገኘውን የኒዩክሌር ሙከራ ጣቢያዋን ማፈራረሷን ገለፀች። በስፍራው የተገኙት ጋዜጠኞችም ጣቢያው በፍንዳታ መፈራረሱን በአካል ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል። በኒዩክሌር ሙከራ ጣቢያው አራት ክፍሎች ያሉ ሲሆን ሶስቱ በፍንዳታ እንዲፈራርሱ  ተደርገዋል። አራተኛው የጣቢያው ክፍል ከረጅም ጊዜ በፊት ከጥቅም ውጭ መሆኑን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል። ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ማብለያ ጣቢያውን ማፈራረሷን የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞች በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱና ሽፋን እንዲሰጡት መጋበዟ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ከማክሰኞ እለት ጀምሮ ጋዜጠኞቹ ከቤጂንግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ሰሜን ኮሪያ ገብተዋል። በዛሬው እለትም ጋዜጠኞቹና የኒዩክሌር ባለሙያዎች በተገኙበት በምድር ውስጥ የሚገኙ ሶስት ክፍሎች በፍንዳታ እነዲፈራርሱ ተደርገዋል። የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አሜሪካ በይፋ ጦርነቷን የምታቆም ከሆነ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቅ እንደማያስፈልግና ወደፊት ስጋት እንደማይፈጥሩ መናገራቸው ይታወሳል። ምንጭ፦ሲ ጂ ቲ ኤን እና ቢቢሲ      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም