ምርጫ ቦርድን ከወገናዊነት የፀዳ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ በሌሎች ተቋማትም ሊተገበር ይገባል -ዶክተር ዲማ ነገዎ

264
አዲስ አበባ ህዳር 17/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሰራርን ከወገናዊነት የፀዳ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ በሌሎች መሰል ተቋማትም ሊተገበር እንደሚገባ አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶክተር ዲማ ነገዎ አሳሰቡ። መንግስት በቦርዱ ላይ እያደረገ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴን የሚያደንቁት ዶክተር ዲማ የቀድሞዋ ዳኛና የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው መመረጣቸው የለውጡ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ ግን በምርጫ ተቋሙ ላይ የተጀመረው ይህ ለውጥ በሌሎች መሰል የዴሞክራሲ ተቋማት ላይም በተመሳሳይ የማይተገበር ከሆነ ነፃ፣ ትክክለኛና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ እንደሚያዳግት ነው ዶክተር ዲማ  ለኢዜአ የገለፁት። ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድና የአገሪቱን የፖለቲካ ባህል ወደእውነተኛ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ከምርጫ ቦርድ ባሻገር ያሉ ሌሎች ተያያዥ ዓላማ ያላቸው ተቋማትንም አብሮ መቀየር ያስፈልጋል። በተለይም ፍትህን ጨምሮ በፍፁም ገለልተኝነት አገርና ህዝብን ማገልገል የሚጠበቅባቸው ተቋማት የለውጡ አካል ሊደረጉ እንደሚገባም ዶክተር ዲማ ገልፀዋል። "በእነዚህ ተቋማት ከአመራር ጀምሮ ያለው የሰው ኃይል አሰራር ገለልተኝነት መረጋገጥ አለበት" ሲሉ ነው ዶክተር ዲማ ያሳሰቡት። ይህ ከተስተካከለ አሁን ቦርዱን እንዲመሩ በመንግስት የተሾሙት ወይዘሪት ብርቱካን ለቦታው የሚመጥኑና ብዙ ልምድ ያላቸው እንደሆኑም ተናግረዋል። የተጀመረውን የዴሞክራሲ ለውጥ ሂደትና መጪውን ምርጫ ስኬታማ ለማድረግ ከምርጫ ቦርዱ አባላት ጀምሮ እስከታችኛው እርከን ያለው ባለሙያ ብቃት ያለውና ሙያውን የሚያከብር የሰው ሃይል ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የሶሻል ዴሞክራቲክ ህብረትና የአረና ፓርቲ አመራሮች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የምርጫ ህጉና አንዳንድ አሰራሮችን ከማስተካከል ጀምሮ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ስለሆነ ለዴሞክራሲ ግንባታው ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብረሃ ደስታ በሰጡት አስተያየት "ወይዘሪት ብርቱካን መመረጣቸው በጣም ጥሩ እድል ነው። ለኢትዮጵያም ፣ለተቃዋሚ ፓርቲዎችም ለገዥ ፓርቲ አባላትም ጥሩ እድል ነው ብዬ ነው የማስበው ግን ፈታኝ ነው ምክንያቱም ምርጫ ቦርድ የተበላሸ ነው ከታች ስለዚህ ብዙ ጥረት ይጠበቃል ትልቅ  ሸክም ነው ያለው ስለዚህ ሁሉም ቢተባበር የተሻለ ነገር ይሰራል ብዬ አስባለሁ˝ ነው ያሉት፡፡ "ከመአከል እስከታች ድምፅ መስጫ ጣቢያ ድረስ  ተስተካክለው፤  ምርጫ ቦርድ ባለሙያ አልነበረውም ለሙው ብሎ የሚሰራ ያልነበረው ተቋም ነው ስለዚህ ለሙያዬ ብለው የሚሰሩ ባለሙያዎችም ተመድበውላት ይህንን ሃላፊነት ትወጣለች ብዬ ነው የማስበው"ያሉት ደሞ የሶሻል ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ  ናቸው፡፡ ከአሁን በፊት በምርጫ ቦርድ ላይ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛነትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን እንዲመሩ ሾሟቸዋል። ይህም አስካሁን ይቀርቡ የነበሩትን ቅሬታዎች ያስቀራል የሚል እምነት በብዙዎች አሳድሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም