"ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ"

146
ሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/ ቀደምት አባቶች የነገርን ስር መያዝ ሲፈልጉ "ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ "ይሉ ነበር። የሰሙት ነገር አልጥምም ካላቸው ደግሞ ይሄ "በሬ ወለደ" አይነት ወሬ ነው በማለት ያጣጥሉታል። ኢንተርኔት ከመፈጠሩ በፊት ወሬ በሰው፣ በራሪ ወረቀቶችን በማሳተም፣ በንግግር ላይ ውሸትን በመደባለቅ ፕሮፓጋንዳ አዘል መልእክቶች ይዘው ይሰራጩ ነበር። ዓለማችን ወደ ቴክኖለጂ አብዮት ከገባች ወዲህ ደግሞ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መረጃዎች ሲተላለፉ ቆይተዋል። በዚህም ህዝቦችን የበለጠ ለማቀራረብና የመረጃ ልውውጥን  ለማቀላጠፍ የሚያግዙ በርካታ የፈጠራ ስራዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ከነዚህ መካከል ደግሞ ገኖ የወጣውና አለምን የበለጠ በማገናኘት ያቀራረበው የማህበራዊ ሚዲያው ነው። ማህበራዊ ሚዲያው የጠፉ ሰዎችን በማገናኘት፣ አገራዊ ለውጦች እንዲመጡ በማገዝና ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡና የለውጥ አብዮቶች እንዲቀጣጠሉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያው እክሎችና ተግዳሮቶች ገጥመውታል። ለምሳሌ ትዊተር ለአይኤስአይኤስ የሽብር ተልእኮ ምልመላ እንቅስቃሴ ሲውል ፌስ ቡክ ደግሞ የሰዎችን የግል መረጃ ለደህንነት አካላት አሳልፎ በመስጠት ተተችቷል። የማሳቹሴትሰ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ባወጡት የጥናት ውጤት በማህበራዊ ሚዲያ ኔትዎርኩ ትዊተር ከሚለጠፉ መረጃዎች መካከል የሃሰት መረጃዎች ከእውነተኛ ዜናዎች ይልቅ የመስፋፋት አቅማቸው በ70 በመቶ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል። ተቋሙ በሶስት ሚሊዮን የትዊተር ተጠቃሚዎች ለተከታዮቻቸው ከተካፈሉ መረጃዎች መካከል በ126ሺህ ጽሁፎች ላይ ከ2006 እስከ 2017 (እአአ) ባደረገው ጥናት መሰረት የሃሰት መረጃዎች ከሃቀኛ መረጃዎች በበለጠ መልኩ በትዊተር ገጾች ላይ ናኝተዋል። ሁሉም አይነት የሃሰት መረጃዎች ከእውነተኛ መረጃዎች በከፍተኛ መጠን እና ፍጥነት የመስፋፋት አቅማቸው ከፍ ያለ ሲሆን ሃሰተኛ የፖለቲካ ጉዳይ መረጃዎች ደግሞ ከሽብር፣ ከተፈጥሮ አደጋዎች፣ ከፋይናንስ ኢንፎርሜሽኖች፣ የተሻለ እንደሚራገቡ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ በአገራችንም የተዛባና ሁከት ቀስቃሽ የሀሰት መረጃዎችን ለማሠራጨት እስከ 100 ሺህ ሊደርሱ የሚችሉ ሐሰተኛ የፌስቡክ አካውንቶች ተከፍተው የጥላቻ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር አድምጠናል፡፡ የጦማሪዎቹ ግብ ደግሞ አገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ መክተትና መበታተን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመንግስት ዓመታዊ ዕቅድ ዙሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፤ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተከፍሏቸው የሃሰት ዜናዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች መኖራቸውን መንግስት ደርሶበታል። ''እነዚህ ግለሰቦች ህዝቡን በማደናገር ከተለያዩ አካላት ጥቅም የሚያገኙ እና የሚከፈላቸው ናቸው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ያልታወቁ ግለሰቦችን ሃሳብ ከመቀበል እንዲታቀቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሆኖም የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው ለውሸት ዜናዎችና መረጃዎች ስርጭት ሰለባ ሆኗል። በኢትዮጵያም የውሸት ዜናዎች ለሰላም መጥፋትና ለብጥብጥ መከሰት የራሳቸውን ሚና በመጫወት ግለሰቦችንና ተቋማትን ሰለባ አድርገዋል። አገርንም ለኪሳራ ዳርገዋል። የውሸት ዜና ምን ማለት ነው የውሸት ዜናዎች ሆን ተብለው የሚፈጠሩ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎች ናቸው። የውሸት ዜናዎች የሚፈጠሩት ሰዎችን ለማሳሳት፣ ለአመጽ ለማነሳሳትና ለማወናበድ ታስበው ሲሆን የተለያዩ መንግስታትም የህዝብን ሃሳብና የተቃውሞ አቅጣጫ ለመቆጣጠር በተለያዩ ጊዜያት ተጠቅመውበታል። ከዚህ ቀደም የውሸት ዜናዎችን ማሰራጨት ከባድ የነበረ ቢሆንም በተለይ የሶሻል ሚዲያው አብዮት ከተከሰተ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ስርጭቱ ጨምሯል። በመረጃ መዋቅር ውስጥ ሰባት አይነት የውሸት ዜናዎች መኖራቸውን ሚሲሲፒ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በድረ ገጹ ያሰፈረው የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪማክ ኮሌጅ የሚዲያ ፕሮፌሰር የሜሊሳ ዚምዳርስ ጥናት ያሳያል። 1- ፉገራ፤ ይህ ዓይነት የውሸት ዜና በሌላ አጠራር ኩምክና የምንለው ሲሆን ሰዎችን ከማሳቅ እና ከማዝናናት ያለፈ ሌላ ዓላማ የለውም። 2-አሳሳች የመረጃ ይዘቶች፤ እነዚህ ደግሞ ሰዎች ትከክለኛውን መረጃ እንዳያገኙ ታስቦ ለማሳሳት የሚፈጠሩ ናቸው። ብዙ ጊዜ ትክክለኛ መረጃዎችን በማጣመም አንድን ሰው ወይም ተቋም ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞከርባቸው ናቸው። 3-አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች፤ እነዚህ ደግሞ የዜና መረጃ ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉ ሰዎችን ወይም ደግሞ የዜና ተቋማትን በመምሰል/በማስመሰል የሐሰት መረጃዎችን ለማሰራጨት የሚሞክሩ ናቸው። 4- የፈጠራ ወሬ፤ ይህ ደግሞ ዜናው መረጃው ከኋላው ምንም አይነት የእውነት መሰረት የሌለው እና መቶ በመቶ የፈጠራ ወሬ ነው። ይህም ብዙዎችን ለማታለል ወይም ለመጉዳት ታስቦ የሚፈጠርና የሚሰራጭ ነው። 5- ሐሰተኛ ግንኙነት፤ ይህ ደግሞ ዜናው /የመረጃው ርዕስ የሚጠቁመው ሌላ ነገር ሆኖ ሳለ ከውስጥ ያለው ፍሬ ነገር ግን ከርዕሱ ጋር ፍጹም የማይገናኝ ነው። ብዙዎቹ ሰውን ሊስብ የሚችል አርዕስት ይለጥፉና ከውስጥ ያለው ፍሬ ሃሳብ ግን ፍጹም ከርዕሱ ጋር የማይገናኝ ይሆናል። 6- ሐሰተኛ ዐውድ፤ በዚህ ጊዜ ዜናው /መረጃው ትከክለኛ እና ተዓማኒ ይሆንና የገባበት ወይም የተተረጎመበት ዐውድ ግን ፍጹም የተሳሳተ ይሆናል። በአብዛኛው በዐውድ አረዳዳችን ስለሚወስን ምንም እንኳን መረጃው እውነተኛ ቢሆንም የገባበት ዐውድ ከተሳሳተ ግን የምንሰጠው ትርጉም የተሳሳተ ይሆናል። 7-የተጣመመ መረጃ፤ አንድ እውነተኛ መረጃን ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱት ተደርጎ ሲጣመም በዚህ ጎራ ውስጥ ይካተታል። መረጃውን በመቆራረጥ፣ ቆርጦ በመቀጠል ወይም ቅደም ተከተሉን በማዛባት ሊቀርብ ይችላል። የሐሰት መረጃን ማስወገድ ከፈለጉ የሚከተሉትን አማራጮች መከተል እንደሚጠቅም ካልቸራል ኮሌክቲቭ የተሰኘ ድረ ገጽ ጠቅሷል። እነሱም ሁሉንም ዜና ወይም መረጃ ማንበብ፣ የመረጃውን ምንጭና ተአማኒነት መመርመር፣ የጸሐፊውን ማንነትና ተቀባይነት መመርመር፣ የተጻፈበትን ቀን ማረጋገጥ እና በመረጃው ላይ ተጨማሪ ምንጮችን ፈልገው ማረጋገጥ ናቸው። የሐሰት ዜናዎች ለምን ይፈጠራሉ የሚዲያ ተንታኝና ባለሙያ የሆነችው ክሌር ዋርድል የሐሰት ዜናዎችን ስርጭት ምክንያቶች እንደሚከተለው አስቀምጣቸዋለች፤ 1- ደካማ ጋዜጠኝነት፤ ይህ ተገቢውን የሙያ ስነ ምግባር ተከትለው ዜናዎችን በአግባቡ የማያጣሩ፣ ነገሮችን በሐሰት የሚያገናኙ፣ አሳሳች የመረጃ ይዘቶችን የሚያቀብሉ እና ሐሰተኛ ዐውድ የሚፈጥሩ ጋዜጠኞችን ያጠቃልላል። 2- ሰዎችን ለመኮመክ የሚቀርቡ፤ እነዚህ ለቀልድ ተብለው የሚቀርቡ ሲሆን አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች እና የፈጠራ ወሬን ሊያካትቱ ይችላሉ። 3- ሰዎችን ለማተራመስ/ለማናደድ፤ ይህን ዓላማ ይዘው የሚነሱ ሰዎች ከላይ ካየናቸው መካከል አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች፣ የተጣመመ መረጃ እና የፈጠራ ወሬን ይጠቀማሉ። 4- ከፍተኛ ፍላጎት፤ ይህ ደግሞ ዜናዎችን ለሌሎች ለማጋራት ከሚኖር ከፍተኛ ጉጉት የሚመነጭ ሲሆን በዚህ ምክንያት ዜናዎችን የሚጋሩ ሰዎች ሐሰተኛ ዐውድ ያጠቃቸዋል። ይህም ማለት ለማጋራት ከመቸኮል የተነሳ መረጃው ሊተረጎምበት የሚገባውን ዐውድ ባለማጤን ለሰዎች ያጋራሉ። 5- ጭፍን ድጋፍ፤ ይህ ደግሞ ለአንድ ግለሰብ ወይም ተቋም ከሚኖራቸው ጭፍን ድጋፍ አንዳንዴም ጭፍን ጥላቻ የተነሳ አሳሳች የመረጃ ይዘቶችን እና ሐሰተኛ ዐውድ ይጠቀማሉ። በዚህም የሚደግፉትን ተቋም ከጥቃት ለመከላከል ወይም የሚጠሉትን ለማጥቃት ካልሆነም ከተገቢው ዐውድ ውጭ ለራሳቸው እንዲያመች አድርገው በመተርጎም ይጠቀሙበታል። 6- የገንዘብ ትርፍ፤ እነዚህ ደግሞ የአንዳንድ ሰዎችን ወይም ተቋማትን እይታ ለመሳብ፣ የህትመት ሚዲያ ባለሙያዎች ደግሞ ለገበያ እንዲያመቻቸው በማሰብ ሐሰተኛ ግንኙነቶችን በማቀናጀት፣ ተአማኒነት ያላቸውን ተቋማት ስም በመስረቅ ወይም በማስመሰል እና የፈጠራ ወሬዎችን የመጠቀም መንገድን ይከተላሉ። 7- የፖለቲካ የበላይነት፤ አንዳንድ ሰዎች ወይም ተቋማት የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት ሲሉ ሐሰተኛ የመረጃ ይዘቶችን፣ ሐሰተኛ ዐውድ፣ የተጣመመ መረጃ እና የፈጠራ ወሬ ይጠቀማሉ። 8- ፕሮፓጋንዳ፤ ሰዎችን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ አካላት አሳሳች የመረጃ ይዘቶች፣ ሐሰተኛ ዐውድ፣ አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች፣ የተጣመመ መረጃ እና የፈጠራ ወሬን ይጠቀማሉ። የማህበራዊ ሚዲያ ዜናን እንዴት እንከታተል በማህበራዊ ሚዲያ ዜናዎችን የምናገኝና የምንከታተል ከሆነ በቅድሚያ ዜናዎችን መምረጥ መልመድ አለብን። በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ማወቅ የማይታሰብ በመሆኑ የምንፈልጋቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ብቻ መርጠን ማንበብ አለብን። ሁለተኛ በማህበራዊ ሚዲያ የምናደንቃቸውንና ተቀባይነት ያላቸውን ግለሰቦችና አስተያየታቸውን መምረጥ ነው። መረጃን የሚወዱ ጥሩ ትንተና የሚሰጡ እና ለእውቀት ፍላጎት ያላቸው አልፎም የበለጠ እንድንመረምርና እውቀትን እንድንገበይ የሚያደርጉንን ሰዎቸ መወዳጀት ጥሩ ነው። ይህም የአስተሳሰብ አድማሳችንን ለማስፋትና ጠያቂ ስብእና እንዲኖረን ይረዳናል። በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ዜና የሚያቀብሉ ታማኝ ምንጮችን መምረጥና ማግኘት ነው። በተለይ ደግሞ ”እንዲህ ተፈጠረ” አይነት ያልተጨበጠ ዜና የሚያራግቡትን ሳይሆን በጉዳዩ ዙሪያ በእውቀት የዳበረ ትንተና የሚሰጡ ሰዎችን ፈልጎ መወዳጀት ይመከራል። "ቅንጭብጭብ" መረጃዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ዜናዎችን በማንበብ መረጃ ማግኘት ይመረጣል። ይህን ማድረግ ከቻልን ደግሞ ዜና ማግኘት ብቻ ሳይሆን የበለጠ እውቀት እናዳብራለን። እውቁ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኛ እና የዲጂታል ጋዜጠኝነት ባለሙያ ክሬይግ ሲልቨርማን ባደረገው ጥናት ”የሐሰት ዜናዎች ከእውነተኛ ዜናዎች በበለጠ ፍጥነት ይሰራጫሉ“ ብሏልና በፍጥነት የሚሰራጩ ዜናዎችን መጠርጠርና ማጣራት የመረጃ ተቀባዩ ግዴታ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም