አራተኛው የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር ተጀመረ

55
አዲስ አበባ ህዳር 17/2011 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞችን ቀን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው አራተኛውን የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ  ተጀመረ። በትንሿ ስታዲዮም በሚካሄደው በዚሁ ውድድር የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለቱም ፆታዎች፤ የትግራይ ክልል ደግሞ በወንዶች ብቻ ተሳታፊ ሆኗል። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩን ያዘጋጀው ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ኮሚቴ ጋር በመተባበር ነው። በውድድሩ መክፈቻ በተደረጉ ጨዋታዎች በወንዶች አማራ ክልል አዲስ አበባን 27 ለ 13 ሲያሸንፍ፤ በሴቶች አዲስ አበባ ኦሮሚያን 10 ለባዶ ረቷል። ከህዳር 4 እስከ ህዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ በተሰጠው የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ስልጠና የተሳተፉ ስፖርተኞች በውድድሩ ተሳትፈዋል። ውድድሩ እስከ ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና ስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ባለፈው ዓመት በተካሄደው ሦስተኛው የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር በወንዶች የአማራ ክልል በሴቶች ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ማሸነፋቸው ይታወሳል። ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን ለ21ኛ ጊዜ ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም "አካል ጉዳተኞችን ማብቃት ሁሉን አቀፍነትና እኩልነት" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም