የአሜሪካ መንግሥት የሶማሌ ክልል መንግሥት ለሚያካሂዳቸው የልማት ሥራዎች ድጋፍ ያደርጋል-አምባሳደር ራይነር

68
ጅግጅጋ ህዳር 17/2011 የአሜሪካ መንግሥት የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለሚያካሂዳቸው የልማት ሥራዎች ድጋፍን እንደሚያጠናክር አምባሳደር ማይክል ራይነር  አረጋገጡ። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ከሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስተፌ ሙሐመድ ጋር በጅግጅጋ  ተወያይተዋል። አምባሳደር ራይነር  ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት አገራቸው የክልሉ መንግሥት የሚያከናውናቸውን የትምህርት፣ የውሃ፣ የጤናና የእንስሳት ሀብት ልማት መስኮች ለማገዝ ዝግጁ ነው። የክልሉን መንግሥት የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረትም ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል። የክልሉ አመራር ለአገራዊ የለውጥ ሥራዎችን ቀጣይነት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የመንግሥታቸው ድጋፍ እንደማይለየው ተናግረዋል። አቶ ሙስተፌ በበኩላቸው ከአምባሳደሩ ጋር ያደረጉት ውይይት ክልላዊ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት በአገሪቱ ሕዝቦች መካከል ያለው አብሮነት እንዲጠናከር በመሥራት ላይ መሆኑንም ለአምባሳደሩ መግለጻቸውንም አስታውቀዋል። አምባሳደር ራይነር በክልሉ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታው በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ የተመሰረቱ ፕሮጀክቶችን ይጉበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም