የህክምና ዶክተሮች አገልግሎት መስጠት በማቆማቸው ተቸግረናል—በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት ፈላጊዎች

3969

ጎባ ግንቦት 16/2010 የህክምና ዶክተሮች  ከትናንት ጀምሮ ስራ በማቆማቸው ተገቢውን የህክምና  አገለግሎት በማጣት መቸገራቸውን በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት ፈላጊዎች ቅሬታቸው ገለጹ።

ዶክተሮቹ  በበኩላቸው ስራቸውን  ያቆሙት ሊያሰራ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ስር መጠቃለሉ ይታወሳል፡፡

ከሆስፒታሉ አገልግሎት ፈላጊዎች መካከል ወይዘሮ አስናቀች ሹሚ ለኢዜአ እንዳሉት የህክምና ዶክተሮች ስራ በማቆማቸው ምክንያት  እየተጉላሉ ነው።

“ከካርድ ክፍል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች አሰፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉልን አይደለም ” ያሉት ወይዘሮዋ በቂ መድኃኒት እንደማያገኙም ተናግረዋል ።

ዶክተሮቹ  አገልግሎት መስጠት በማቆማቸው እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ታካሚዎች መቸገራቸውንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም አመልክተዋል፡፡

ከጋሰራ ወረዳ ለተሻለ ህክምና ወደ ሆሰፒታሉ የመጡት አቶ ሀጂ አብዲ በበኩላቸው የህክምና ዶክተሮቹ አገልግሎት በማቆማቸው ምንም ዓይነት የህክምና እርዳታ ባለማግኘት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

” የህክምና ዶክተሮቹ ያለባቸውን አስተዳደራዊ ጥያቄዎች እየሰሩ ማቅረብ እየቻሉ አገልግሎት ማቆማቸው በጣም አሳዝኖኛል” ያሉት ደግሞ ከአጋርፋ ወረዳ ለህክምና የመጡት አቶ መሐመድአሚን ሀጂ አልይ  ናቸው፡፡

የሆስፒታሉ አስተዳደር ከሀኪሞቹ ጋር በመመካከር የህሙማኑን ህይወት ለመታደግ መፍትሄ መፈለግ እንዳለበትም አስተያየት ሰጪው አመልክተዋል።

ከሐኪሞቹ  መካከል ዶክተር ተከተል ጥላሁን በሰጡት አስተያየት ከድንገተኛ የህክምና አገልግሎት ውጪ በሌሎች የህክምና ዘርፎች ላይ ስራ ለማቆም መገደዳቸውን ተናግረዋል።

“ዋናው ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባነው ውል መሰረት ኦቨር ሎድ የሚባል ክፍያ እንዲፈፀምልን ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ለስምንት ወራት ያህል ምላሽ ማግኘት ባለመቻላችን ነው “ብለዋል ።

ዶክተር ተከተል እንዳሉት ሆስፒታሉ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ለህሙማን ለመስጠት የሚያስችል የቤተ ሙከራ መሳሪያ ፤ የኤሌክትሪክ ጄኔሬተር ሌሎችም ለአንድ ሪፈራል ሆሰፒታል የሚያስፈልጉ  የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሟሉና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ያቀረቧቸው  ጥያቄዎች ምላሽ ያለማግኘታቸው ሌላው  ምክንያት ነው፡፡

“ህሙማኑ ከሆስፒታሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት በማጣት  ለከፍተኛ ወጪም እየተዳረጉ ማየት የስራ ተነሳሽነትን ጭምር የሚጎዳ በመሆኑ መስተካከል አለበት” ብለዋል ።

በእናቶችና ህፃነት ክፍል የሚሰሩት ዶክተር ቶማስ ንጉሴ በበኩላቸው “በዩኒቨርሲቲው ስንቀጠር ከመማር ማስተማሩ ስራ በተጓዳኝ ወደ ሆስፒታሉ ለሚመጡ ህሙማን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በየወሩ 3ሺህ 100 ብር እንዲከፈለን ከዩኒቨርስቲው ጋር ውል ገብተን ነበር ” ብለዋል፡፡

እየሰሩ እንዲከፈላቸው ላለፉት ስምንት ወራት ተደጋጋሚ ጥያቄ  ቢያቀርቡም  ትኩረት በማጣቸው ድምፃቸውን ለማሰማት የተመላላሽ ህክምናውን  ስራ ለማቆም መገደዳቸውን  ገልጸዋል።

የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የክሊኒካል ክፍል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሳፊ ሀጂ  ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የህምክና አገልግሎት ፈላጊዎቹም ሆነ ሐኪሞቹ ያነሱት ቅሬታ ትክክልና ለማስተካከልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ያለበትን የቦታ ጥበትና የቁሳቁሰ ችግር ለማቃለል ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመመካከር ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ክፍያው የዘገየው ተጨማሪ በጀት ባለመለቀቁ ምክንያት እንደሆነና  አሁን ግን የተለቀቀ በመሆኑ በመጪዎቹ አስር ቀናት ውስጥ እንደሚከፈል የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አለማየሁ ጆቴ በስልክ በሰጡት ምላሽ ነው፡፡

ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ስር የተጠቃለለው  የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል 14 ስፔሻሊስቶችና ከ40 በሚበልጡ አጠቃላይ ዶክተሮች እንዳሉት ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡