ወደ ባህር ዳር የመጣነው በብሄሮች መካከል የሚረጨውን የጥላቻ እንቦጭ ነቅሎ ለመጣል ነው -ኢንጂነር ታከለ ኡማ

784

ባህር ዳር ህዳር 16/2011 ”ወደ ባህር ዳር የመጣነው በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ነቅለን ልናጠፋ ሳይሆን ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል በብሔሮች መካከል የሚረጨውን የጥላቻ እንቦጭ ነቅሎ ለመጣል ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ  ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባው ይህን ያሉት ዛሬ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ከባህር ዳር ከተማ ወጣቶች  ጋር ወንድማማችነትን ለማጠናከር ታስቦ በባህር ዳር ከተማ  በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በጣና ሐይቅ  ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም  ለማጥፋት ከአዲስ አበባ መምጣት ግዴታ እንጅ እንደውለታ እንደማያስቆጥር ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች የሁሉም ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቅይጥ መሆናቸውን የገለጹት ኢንጅነር ታከለ  የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር በሚደረገው ሂደት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች  በቀጣይ የውይይት መድረኮች በተለያዩ የክልል ከተሞች ያካሂዳሉ።

በመቀሌ፣ አዳማ፣ ሀዋሳና ሌሎች የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ውይይቶች እንደሚደረጉ ኢንጅነር ታከለ አስታውቀዋል።

የአሁኑ ትውልድ አባቶቹ መስዋትነት ከፍለው ዳር ድንበሯን አስጠብቀው ያቆዩለትን ሀገር አንድነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካልሰራ የታሪክ ተወቃሽ እንደሚሆን ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን እንኳን የጣናን እንቦጭ  በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጰያን ሉአላዊነት ሊደፍሩ የመጡ ቀኝ ገዥዎችን አሳፍረን መልሰናቸዋል ያሉት ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ ናቸው።

”ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካና በተለይም ለቀጠናው አገራት ተስፋ ሰጭ በሆነ ተስፋ ላይ ትገኛለች” ያሉት ኃላፊው ብሔር ከብሔር ለማጋጨት እንቅልፍ የማይወስዳቸው አካላት ስላሉ መላው የኢትዮጵያዊ በተለይም ወጣቱ  ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር   የኢትዮጵያ ብሔሮች መነኻሪያ ስለሆነ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ምግባሩ የአገር አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ህዝብና መሪ ድርጅቱ በከፍተኛ ትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ አስፈጻሚ አካላት፣ ወጣቶች እንዲሁም የአማራ ክልል  የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።