ብሄር ተኮር ጥቃት የሚያደርስ ማንኛውንም ሃይል እንታገላለን – የትግራይ ደቡባዊ ዞን ነዋሪዎች

803

መቀሌ ህዳር 16/2011 ብሔር ተኮር ጥቃት የሚያደርሱ ፀረ ሰላም ሀይሎችን  ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን በትግራይ ደቡባዊ ዞን የኦፍላ ወረዳና የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚካሄደውን ብሄር ተኮር ጥቃት በመቃወም በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ዛሬ በኮረም ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

ነዋሪዎች ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንዳሉት በመራራ ትግልና የህይወት መስዋእትነት የተረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና አንድነት በግለሰቦችና ቡድኖች አይፈርስም።

ነዋሪዎቹ ‘‘ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር እንታገላለን፣ የትግራይ ህዝብን ለማዳከም ሆን ብለው ለሚንቀሳቀሱ ማናቸውንም ሀይሎች እንታገላቸዋልን‘‘ የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማስተጋባት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ ከተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የኮረም ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሽዋጋ መሰለ እንዳሉት  የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር እንጂ የማንነት ጥያቄ የላቸውም፡፡

የኮረም ከተማ ነዋሪ ወጣት መንገሻ ተሾመ በበኩሉ በአካባቢያቸው ሁከትና ግርግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ለመታገል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

በማንነት ጥያቄ ሽፋን የህዝቡን ስነ ልቦና የሚያውኩ ሰላም የሚያደፈርሱ ግለሰቦችና ቡድኖችን በጽኑ እንደሚያወግዙ የተናገሩት ደግሞ በሰላማዊ ሰልፉ የተሳተፉት የኮረም ከተማ ነዋሪና የሃይማኖት አባት መልአከ ገነት ንጉስ መኮነን ናቸው።

የፌዴራል መንግስትም ለሰላምና ብልፅግና ለሚዘምሩና ለሚታገሉ ህዝቦች ሊያግዝ እንደሚገባ ነው መልአከ ገነት ንጉስ ያሳሰቡት።

ወጣት ዘነቡ ዳርጌ በበኩሏ ወጣት ዘነቡ ዳርጌ በበኩሏ ”እኛ የምናውቀው ትግራዋይ መሆናችን ብቻ ነው፤ ‘ሳንፈልግ አማራ ናችሁ እያሉ የሚያውኩን ግለሰቦች እኛ ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብም የሚቀበላቸው አይመስለኝም” ብላለች።

”ማንነትና ብሄር እያሉ ለሚያውኩን ተቀባይነት የላቸውም።የኮረምና የኦፍላ ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንጂ የማንነት ጥያቄ እንደሌለው አውቀው እንዲታገሱ እንጠይቃለን” ብላለች።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የኮረም ከተማ ከንቲባ ዳርጌ መረሳ በበኩላቸው ”የወረዳው መስተዳደርና ህዝብ ወደ ግጭት ላለመግባት ሁሉንም ነገር በትእግስት እያሳለፈ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል።