አንድነታችንና ሰላማችንን በማስጠበቅ ለሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተምሳሌት እንሆናለን--- የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

99
ጎንደር ኅዳር 16/2011 አንድነታቸውን በማጠናከርና ሰላማቸውን በመጠበቅ ለሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተምሳሌት ለመሆን እንደሚንቀሳቀሱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ  ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት መነሻ በማድረግ በተማሪዎች የውይይት መድረክና ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ "አንድ ነን ማንም አይለየንም " የሚል መፈክር ይዘው ለሰላም ያላቸውን አቋም በዩኒቨርሲቲው ተዘዋውረው የገለጹት ተማሪዎቹ፣ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥላቻ በውስጣቸው እንዲበቅል የሚያደርጉ አካላትን አጥብቀው እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የባዮ ኬሚስትሪ ተማሪ የሆነው ዮሴፍ ዘላለም ለኢዜአ እንደተናገረው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ፍቅርንና አንድነትን እንጂ ጥላቻንና ዘርን መሰረት ያደረገ ትንኮሳ በተማረ አዕምሮ ውስጥ ሊፈልቅ አይገባም፡፡ "ከአካባቢያችን ወጥተን መማራችን የሌሎች ታሪክ፣ ባህልና ወግ አውቀን እርስ በእርስ የምንከባበርበት፣ ፍቅርና አንድነት የበለጠ የምናጠናክርበት እንጂ ለአደጋ እንጋለጣለን በሚል ስጋት ተሸማቀን ልንኖር አይደለም" ብሏል። ይሄንን በሚያደርጉ አካላት ላይ መንግስት አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም የጠቆመው ተማሪ ዮሴፍ ሰላማቸውን በመጠበቅ ለሌሎች አርአያነት ያለው ተግባር ለመፈጸም እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡ ተማሪ ወንድወሰን ዳና በበኩሉ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማደናቀፍና ተማሪዎችን እርስ በእርስ ለማጋጨት አጀንዳ የሚቀርጹ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጿል፡፡ በተማሪዎች መካከል የተደረገው የምክክር መድረክና የተፈጠረው የአንድነት ስሜት እንዳስደሳት የገለጸችው ደግሞ ተማሪ ሜላት ቱሉ ናት ፡፡ ተማሪዋ " 'በመካከላችን ያለ የጥላቻ ግንብ ይፍረስ፣ የፍቅር ድልድይ እንገንባ' የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን መልዕክት ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል" ብላለች። ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ፍቅርን በመስበክ አንዱ ብሔር ለሌላው ብሔር ስጋት ሳይሆን ወንድም መሆን እንዳለበት በተጨባጭ በማረጋገጥ ምሳሌ ለመሆን መስራት እንዳለባቸው ጠቁማለች፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ሕብረት ተወካይ ተማሪ ዮሐንስ ተሻገር በበኩሉ ተቋሙ "የሰላም ዩኒቨርሲቲ" መሆኑን ጠቅሶ ይህን ስሙን በተግባር ለማረጋገጥ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሁሉም ሰራተኞች ከዘረኝነት አስተሳሰብ ተላቀው ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማምጣት እንዳለባቸው አመለክቷል፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ቀናት በዩኒቨርሲቲው ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ዳግም እንዳይከሰት ተማሪዎች ትስስራቸውን ከማጠናከር ባለፈ  ከመጡበት የትምህርት ዓላማ ውጭ መንቀሳቀስ እንደሌለባቸውን ነው የገለጸው፡፡ "የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ መንቀሳቀስ የለብንም" ያለው ተወካዩ ተማሪዎች ከነገ ጀምሮ ትምህርታቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም