የአፋር ክልልን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለፀ

97
ሰመራ ህዳር 16/2011 የአፋር ክልልን  ሰላም  በዘላቂነት ለማስጠበቅ የተጀመረውን የተቀናጀ ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ የጸጥታ  ባለድርሻ አካላት ገለፁ፡፡ በክልሉ በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ አመት የሰላምና ጸጥታ እቅድ  አተገባበር የገመገመ የውይይት መድረክ ትናንት በሰመራ ከተማ ተካሄዷል፡፡ የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአፋር ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን አኒሳ እንደተናገሩት በክልሉ ያለውን አስተማማኝ ሰላም የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች እየተከሰቱ ነው፡፡ ይሁንና የክልሉና የፌዴራል የጸጥታ አካላት አንዲሁም የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ንቁ ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት በክልሉ ግጭትና ሁከት አንዳይከሰት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በመሆኑም ይህን ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል በተለይም በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች በህብረተሰቡ ውስጥ ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎችና ዝንባሌዎችን ፈጥኖ በማረም ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ የሰሜን ምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ጄኔራል ዘውዱ በላይ  በበኩላቸው እዙ የክልሉን የጸጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ባሳተፈ መንገድ የሀገሪቱን ሰላምና ልማት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን እየመከተ ነው፡፡ በተለይም ክልሉ ዋነኛ የሀገሪቱ መግቢያና መውጫ በር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ሰላም ማረጋገጥ፤ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚከሰቱ ግጭቶን መቆጣጠርና ህገ-ወጥ የሰዎችና የመሳሪያ ዝውውርን እንዲሁም ኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ የውይይት መድኩም በየደረጃው ያለው የጸጥታ መዋቅርም ሆነ ባለድርሻ አካላት በቀጣይ ለክልሉ ሰላምና ለህብረተሰቡ ደህንነት ጠንቅ የሆኑ ስጋቶችን ተቀናጅቶ በመከላከል፤ የእስካሁን የስራ ሂደቶች በመገምገምና ክፍተቶችን በማረም ጠንካራ ጎኖች አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያግዙ ግብአቶች የተገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የገቢ-ረሱ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀሰን አሊ እንደገለፁት ደግሞ ዞኑ ከአማራ፣ ኦሮሚያና ሱማሌ ክልል ጋር የአስተዳደር ወሰን የሚጋራ ሲሆን በአዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶች እንዳይከሰቱ የሚያግዙ ስራዎችን በማከናወን የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ማድረግ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በወረዳው ህገወጥ ገንዘብና መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ከሚመከታቸው የወረዳ፣ የክልሉና በአቅራቢያው ከሚገኙ የፌዴራል መንግሰት የጸጥታ አካላት ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራሮችን የበለጠ አጎልብቶ ለመቀጠል አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የውይይትና ግምገማ መድረኮች ክፍተቶቻቸውን ለማረምና ጥንካሪያቸውን ለማጎልብ እደሚያግዛቸው አስረድተዋል፡፡ ከአደአር ወረዳ የመጡት የሃገር ሽማግሌ አቶ አህመድ ዋሪ ወረዳቸው ከአማራ ክልል ባቲ ወረዳ ጋር የሚዋሰንና ከ2007 አ.ም ጀምሮ በሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች የሰዎች ሞትና የከብት ስርቆት በተደጋጋሚ እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡ በወረዳቸው በኩል በእንደዚህ አይነት ወንጀል ላይ የተሳተፉ አካላትን ህብረተሰቡ አሳልፎ ለህግ በማቅረብ ኃላፈነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልፀው በባቲ ወረዳ በኩልም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም