በትግራይ ማዕከላዊና ደቡባዊ ዞኖች ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ

88
አክሱም /ማይጨው ህዳር 16/2011 የህግ የበላይነትን ሽፋን በማድረግ የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክ የሚደረግ እንቅስቃሴን እንደማይቀበሉ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የስድስት ወረዳ ነዋሪዎች ዛሬ ባካሄዱት በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ። በዛሬው ዕለት ሰልፉን ያደረጉት የአክሱም፣ የአድዋና አብዪ አዲ ከተሞችና የላዕላይ ማይጨው፣ የገጠር አድዋና የቆላ ተምቤን ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው። " ነዋሪዎቹ  ህግ መንግስቱ ይከበር ፣ ፍትሕ በሁሉም በእኩልነት ይተግበር ፣ በውጭ ጣልቃ ገብነት የትግራይ ህዝብ ለማንበርከክ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም ፣ የክልሉ መንግስት መግለጫ እንደግፋለን " የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች መተባበራቸው አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል። በሰልፉ የተገኙት የአክሱም ከተማ ነዋሪ መምህር ተወልደመድህን የዕብዮ እንደገለጹት የህግ የበላይነት ሽፋን በማድርግ ያልተገባ ተግባር  እንዳይፈጸም መልዕክት ለማስተላለፍ  ሲሉ ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል። የሀገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅና ህገ መንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርአቱን ለማጠናከር ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። በአክሱም ከተማ የሐየሎም ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ አርዓዶም በበኩላቸው "የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክ የሚደረግ ሴራ እንዲቆም ድምጻችን ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተናል" ብለዋል። የጀግኖችን ፈለግ በመከተል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሀገራዊ አንድነትና እኩልነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት። በአክሱም ከተማ በተደረገው ህዝባዊ ሰልፍ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ተስፋይ የትግራይ ህዝብ ፌዴራላዊና ህግ መንግስታዊ ስርአቱ እንዲረጋገጥና እንዲከበር ሲታገል መቆየቱን አስታውሰዋል። የህግ የበላይነት ማስከበር አግባብ ቢሆንም በእዚህ ሽፋን የሀገርና የህዝብ ልማትና ስላም ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። "የህግ የበላይነት ለማስከበር ሁሉንም በእኩል ዓይን ማየት ይገባል" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የህግ የበላይነትና ህገ መንግስቱን ማስከበር ለሀገር ሉአላዊነትና ለህዝቦች ዋስትና መሆኑን ተናግረዋል። በሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትግል የተረጋገጠው ህገ መንግስታዊ ስርአት ሁሌም ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ህዝቡ ሁሌም በጽናት እንዲቆም ጠይቀዋል። "የትግራይ ህዝብ የታገለለት ዓላማ የኢትዮጵያን አንድነት በማረጋገጥ ሰላም እንዲሰፍን እና የህግ የበላይነት እንዲከበር እንጂ በብሔር ላይ ያነጣጠረ ልዩነት እንዲፈጠር አይደለም" ያሉት ደግሞ የአክሱም ከተማ ከንቲባ አቶ ኤልያስ ካሕሳይ ናቸው። ህዝብ ተረጋግቶ ፊቱን ወደልማት እንዳያዞር በተለያዩ መንገዶች በመተንኮስ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመፈጸም የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል። ሦስት የገጠር ወረዳዎችን ጨምሮ ዛሬ በአክሱም፣ ዓድዋና ዓብይ ዓዲ ከተሞች በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ተሰታፊ መሆናቸው ተመልክቷል። በተመሳሳይ ዜና በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ የአላማጣ፣ ኮረም፣ እንዳመሆኒ፣ የራያ ዘቦና አምባላጄ ወረዳ ነዋሪዎች ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። ነዋሪዎቹ በሰልፉ ላይ ባሰሙት መፈክር ማንነትንና ህግን ሽፋን በማድረግ በብሔር ላይ የሚካሄድ ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም ጠይቀዋል። ነዋሪዎቹ ይህን የጠየቁት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በቅርቡ ላወጣው መግለጫ ድጋፋቸውን ለመስጠት በየአካባቢያቸው ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ነው። "የራያ ህዝብ የመልካም አስተዳደርና ልማት እንጂ የማንነት ጥያቄ የለውም ፣ በክብራችንና ማንነታችን አንደራደርም፣ በህዝቦች ትግል የተገኘውን ሰላም በማንም አይደናቀፍም" የሚሉና ሌሎች መፈክሮችንም ነዋሪዎቹ አሰምተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም