የወላይታና የሲዳማ ህዝቦች ሰላም ወዳድ፣ ፍቅር ያላቸውና ተለያይተው መኖር የማይችሉ ናቸው.... ገለልተኛ አስታራቂ አባቶች

92
ሀዋሳ ህዳር 16/2011 የወላይታና የሲዳማ ህዝቦች ሰላም ወዳድ፣ ጠንካራ ፍቅር ያላቸውና ተለያይተው መኖር የማይችሉ መሆናቸውን አረጋግጠናል ሲሉ የሲዳማና ወላይታ ገለልተኛ አስታራቂ አባቶች ገለጹ፡፡ በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየው አብሮነትና አንድነት ከጠፋ አገሪቱን ወደሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ላይ ማድረስ ስለማይቻል ህዝቡ ሰላምና አብሮነቱን ማጠናከር እንዳለበት አባቶቹ መክረዋል። በወላይታና ሲዳማ ተወላጆች መካከል ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት ወደሰላም ለመመለስ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ የእርቅ ሂደት ማለፋቸውን የተናገሩት አስታራቂ አባቶቹ ሁለቱ ህዝቦች ሰላም ወዳድ፣ እርስ በርስ ፍቅር ያላቸውና መለያየት እንደማይችሉ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። የገለልተኛ አስታራቂ ኮሚቴው ሰብሳቢ መጋቢ ጌቱ አያሌው እርቅ ለማውረድ በተደረገው ጥረት በሁለቱ ወንድማማች ህዝብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው የጥል ግድግዳ መፍረሱንና በእዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ "ሁለቱን ህዝብ ለማስታረቅ እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ወቅት አልፈናል" ያሉት መጋቤ ጌቱ፣ ሠላምና እርቅ የማይፈልጉ ሁለቱንም ብሄር የማይወክሉ ግለሰቦች በአካልና በማህበራዊ ሚዲያ ስም የማጥፋት፣ የማስፈራራትና ተስፋ የማስቆረጥ ሥራዎችን ቢሰሩም እርቁ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል። ዕርቀ ሰላሙን ለማውረድ ከሁለቱም ብሔር አገር ሸማግሌዎች ጋር ለአራት ወራት የመከሩ ሲሆን በእዚህም ሁለቱም ህዝቦች ሰላም ወዳድ ከመሆናቸው ባለፈ እርስ በርስ የሚፋቀሩና ተለያይተው መኖር የማይችሉ ናቸው። በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነትና አንድነት በመጠበቅ በአገሪቱ የሚፈለገውን እድገት ለማምጣት ተረባርቦ መስራት እንደሚገባም  አሳስበዋል፡፡ የሃዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ መላከ ምህረት ቆሞስ አባ ጌዲዮን ብርሃን በበኩላቸው መነጣጠል የማይችሉ ሁለቱ ህዝቦች በመታረቃቸው ከማንም በላይ የተለየ ደስታ እንደተሰማቸው ነው የገለጹት። በእርቅ ሂደት ውስጥ የሲዳማና የወላይታ አገር ሸማግሌዎች ሠላም ለማውረድ ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸውንና የክልሉና የሁለቱ ዞን የመንግስት አካላትም ላሳዩት ቀና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የእርቀ ሠላም ጉባኤው ለኢትዮጵያውንና ህዝብን ለማበጣበጥና የአገሪቱን ሠላም ለማድፍረስ ደፋ ቀና ለሚሉ አካላት ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ "ኢትዮጵያውያን ያለንን አብሮነትና አንድነት ካጣን ወደምናስበው የእድገት ደረጃ መድረስ ስለማንችል ቆም ብለን ልናስብ ይገባል" ሲሉም መላከ ምህረት ቆሞስ አባ ጌዲዮን አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት ፍቅርና አንድነቱን ጠብቆ በማቆየት ሰላምና ልማቷ የተረጋገጠ አገር ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት አውቆ ለእዚያ መንቀሳቀስ እንዳለበትም መክረዋል፡፡ ከአላህ ዘንድ የተሰጣቸውን ትልቅ ኃላፊነት በስኬት በማጠናቀቃቸው ሀሴት እንደተሰማቸው የገለጹት ደግሞ የደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የገለልተኛ አስታራቂ ኮሚቴ አባል ሃጂ አህባበብ አባ ጀማል ናቸው፡፡ የሲዳማና የወላይታ አገር ሸማግሌዎች ሰላም የሚሹ ፣ የተጎራበቱ፣ የተጋቡና የተዋለዱ መሆናቸውን ያረጋገጡበት የእርቅ ሂደት መሆኑን የገለጹት ሃጂ አህባበብ፣ ሰላም አንዲወርድ እንደኮሚቴ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአብሮነትና ለሠላም ቅርብ በሆኑ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተከሰተው መራራቅና አለመተማመን በአሁኑ ወቅት መፈታቱንና በቀጣይም ለዘላቂ ሰላም በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በሃዋሳና በሶዶ ከተማ የተካሄደው የሁለቱ ህዝቦች የይቅርታና እርቅ ኮንፈረንስ በገለልተኛ አስታራቂ ሽማግሌዎች ላለፉት አራት ወራት የተለያዩ ሂደቶችን ያለፈ መሆኑን ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም