በለውጡ ሂደት አዎንታዊና አሉታዊ አመለካከቶችን አጣጥሞ መሄድ ያስፈልጋል-አቶ ሌንጮ ለታ

445

አዲስ አበባ ህዳር 16/2011 ለለውጡ ስኬት አንድ ዓይነት አመለካከት ያለው ህዝብ መፍጠር ሳይሆን የብዙሃኑን አመለካከቶች አጣጥሞ መሄድ አዋጭ መሆኑን አቶ ሌንጮ ለታ ተናገሩ።

አቶ ሌንጮ ይህን ያሉት ትናንት ተጀምሮ ዛሬም በቀጠለውና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) አዳራሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ልሂቃን የተሳተፉበት ውይይት ማጠቃለያ ላይ ነው።

አቶ ሌንጮ ብዝሃ አመለካከቶችን ከአገሪቱ ሉአላዊነትና ከብዙሃኑ ህዝብ ጋር አጣጥሞ መሄድ አስፈላጊ መሆኑንም በአጽእኖት ገልጸዋል።

ይህንን ለማድረግ የሽግግር ፍትህን ማረጋገጥ ፤ ያጠፉ የሚቀጡበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበትና ተመሳሳይ ድርጊት የማይደገምበት ስርዓት መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል።

በመሆኑም ሃላፊነትና ተጠያቂነትን በማረጋገጥና የህዝብ ተሳትፎ በማሳደግ ቀድሞ የነበረውን “የመከልከልና  የመፍቀድ የፖለቲካ ሂደት ማስቀረት ይኖርብናል” ሲሉም ተናግረዋል።

ይህም አዎንታዊ የሆነውን አስተሳሰብ ወይም የመደገፍና የመስማማት አመለካከት ብቻም ሳይሆን አሉታዊ አመለካከት ያላቸውን ሰዎችንም አቅፎ መሄድንም ይጠይቃል።

ግልጽና ግልጽ ያልሆኑ “የቡድን ፍረጃዎችንም ልናስወግድ  ይገባናል” ሲሉም በማጠቃለያው ላይ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙሃንም የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ጥሪ ቀርበዋል።