በሀገሪቱ ያለውን እምቅ የማዕድን ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

536

አዳማ ህዳር 16/2011 በሀገሪቱ ያለውን እምቅ የማዕድን ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ  እንደሚገባ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አሳሰበ።

በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት ባለፉት ሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደው “የማዕድን ስራዎች ምክር ቤት 1ኛ መደበኛ ልዩ ጉባኤ” ተጠናቋል።

በጉባዔው  ማጠቃለያ ላይ  የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዳስታወቁት የማዕድን ሥራ በባህሪው ሰፊና ውስብስብ ተግባራት የሚከናወንበት ስለሆነ የሁሉንም አካላት ቅንጅትና ርብርብ ይጠይቃል።

ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ደካማ በመሆኑና የአስፈፃሚ አካላት አለመናበብ፣ የቅንጅት ማነስና በግልጸኝነት ችግር ሀብቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት እንዲመረቱ በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የማዕድናት ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በመከላከል የውጭ ምንዛሪ አቅምን ለማሳደግና ለዜጎችም ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተመላክቷል።

የማዕድን ልማት የህብረተሰቡንና የአካባቢውን ደህንነት በጠበቀና የህዝቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መንገድ በዘላቂ የልማት መርህ ሊለማ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰፋ ኩምሳ ዘርፉ በዓለም  አቀፍ  ደረጃ   ተወዳዳሪ  እንዲሆን  ተስማሚ  ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ገልጸው በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የማዕድን ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ግብዓት እየተሰባሰበ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በዘላቂነት ለማረጋገጥም የአገልግሎት  አሰጣጥን በየደረጃው ማዘመንና  ግልጽ  አሰራር  ማስፈን ወሳኝ  መሆኑን ጠቁመዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል የሻኪሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ጃራ በማዕድን ልማት ዙሪያ በየደረጃው ተናቦ ባለመሰራቱ ምክንያት የህዝብ ቅሬታን ከማስከተሉም ባለፈ ግዙፍ የማዕድን ኩባንያ እንዲዘጋ ማድረጉን ገልጸዋል።

መድረኩ የቅንጅት አሰራርን ለማስፈንና የችግሮችን መንስኤ ነቅሶ በማውጣት የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀመጠ በመሆኑ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀልዶ አቡቤና በበኩላቸው በዘርፉ በህግ አስገዳጅነት ላይ የተሰራ ስራ ባለመኖሩ ከአልሚዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

በማዕድን ጥናት ላይ የግልጸኝነት ችግር በመኖሩም የግጭት መንስኤ እየሆነ መምጣቱን የሚናገሩት ኃላፊው አልሚዎችም የሚጠበቅባቸውን እያበረከቱ ስላልሆነ በቀጣይ ይህ ችግር እንዲፈታ ጠይቀዋል።

ይህንን ችግር ለማቃለል የመደጋገፍ አሰራር፣ አደረጃጀት፣ አቅርቦትና በክህሎት ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ከክልሎች ጋር በመሆን የተለያዩ ስልቶች ተግባራዊ እንደሚሆኑ በሚኒስቴሩ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በአምላክ አለማየሁ አስታውቀዋል።

አላቂ የተፈጥሮ ሀብት ከሆነው ከማዕድን ምርትና ግብይት መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ የክልልና የፌዴራል ፈቃድ ሰጭ ባለሥልጣናት  በሥራ ላይ ባሉት ሕጎች መሰረት ብቻ ኃላፊነታቸውን  በአግባቡ እንዲወጡም  አስገንዝበዋል።

በሕግ የተደነገጉት የማዕድን ዓይነቶች የግንባታ፣ የኢንዱስትሪ፣ ብረት ነክ፣ የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናት  መሆናቸውን ከመድረኩ የተገኘው መረጃ ያመልክታል፡፡