የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ይሰራል – የፓርቲው ሊቀመንብር

531

ሰመራ ህዳር 16/2011 የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልም ሆነ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆን የፓርቲው ሊቀመንብር አቶ ስዩም አወል ገለጹ፡፡

ከአንድ ሺህ በላይ አባላት የተሳተፊበት ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀምሯል፡፡

አቶ ስዩም አወል በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ባለፉት አመታት ድርጅቱ የአፋርን ህዝብ በሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ዙሪያ አስተባብሮ በመምራት አበረታች የልማት ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡

ይሁንና የተመዘገቡት ስኬቶች ድርጅቱ ከተጣለበት ኃላፊነትና ከህብረተሰቡ የልማት ፍላጎት አንፃር ብዙ የሚቀረው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኮንፈረንሱ አላማም በአመራሩ መካከል የተፈጠረውን የአመለካከት ልዩነት በማረም በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ዳር እንዲደር ፓርቲው የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት በሚችልበት ዙሪያ ለመወያየት ነው፡፡

በተጨማሪም ፓርቲው በህብረተሰቡ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሪፎርም ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝት የሚያሳይበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንርና የፖሊት ቢሮ ኃላፊ አምሳደር ሀሰን አብዱልቃድ በበኩላቸው ፓርቲው ባለፉት አመታት በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በመፍታት እራሱን እያረመ የመጣ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተለይም በ2009 ከከፍተኛ  እስከ ታችኛው አመራር ድረስ በጥልቀት በመገምገም  ወደስራ ቢገባም በአመራሩ ዘንድ የሚፈለገውን ያክል ውጤት አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኮንፈረንሱ በቅርቡ ከሚካሄደው ሰባተኛ የፓርቲ መደበኛ ጉባኤ በፊት ፓርቲው ጠንካራና ወጥነት ያለው አንድነት በመፍጠር ህዝቡ የጣለበትን ኃላፈነት ለመወጣት የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል፡፡

ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የህግ የበላይነት፣ የአባላት ስነምግባር ሁኔታዎችና ሌሎች ነጥቦች የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በሁለት ቀናት ቆይታቸው በትኩረት የሚወያይባቸው ርእሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡