በትግራይ ክልል የሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

158
ሁመራ ህዳር 16/2011  በትግራይ ክልል የሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪዎች ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በቅርቡ ላደረጉት ንግግር ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ። ነዋሪዎቹ ለምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ትናንት በተሽከርካሪዎች የጀመሩት ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ወጣቶችን ጨምሮ በሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል። በሰልፉ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች፣ ማህበራትና ነዋሪዎች "የትግራይ ህዝብ ታሪክ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ታሪክ የለውም ! ፣ የህግ በላይነት ይከበር! ፣ በሙስና የተጠረጠሩ በቁጥጥር መዋላቸውን ብንደግፍም በሙስናና ኢሰብአዊ አያያዝ ሽፋን ብሔር ተኮር ጥቃት ይቁም!፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቁም !" የሚሉ የተለያዩ መፈክሮች አሰምተዋል። የትግራይ ህዝብ ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ የቆመ ነው ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል። መንግስት የህግ በላይነት ለማስከበር የጀመረው እንቅስቃሴ እንደሚደግፉት የገለጹት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ፣ ህግን የማስከበር ሥራው በሁሉም አካላትና ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲተገበር ጠይቀዋል። በሰልፉ ላይ የተሳተፉ የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ነዋሪ አቶ ተመስገን ካሕሳይ "የትግራይ ህዝብ በእኩልነትና በፍትህ ያምናል፤ ለዓመታት የታገለውም የህግ በላይነት እንዲረጋገጥ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ወጣት የዕብዮ ኃይሉ የተባለ ሌላው የወረዳው ነዋሪ በበኩሉ "እኛ ህግ የጣሰና በሙስና የተዘፈቀ መደበቂያ አንሆንም፤ መጠየቅ ያለባቸው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች ያሉ በመሆኑ ህግ የማስከበር ሥራ በሁሉም ሊተገበር ይገባል" ብሏል። የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር ሆኖ መታገሉን ገልጾ አሁንም የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረጉ ጥረቶች ማንኛውም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል። የሰቲት ሑሞራ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰለሞን አረጋይ በበኩላቸው "ዶክተር ደበረጽዮን ያደረጉት ንግግር ሰላምና ልማትን የሚፈልግ ማንኛውንም ብሔር የሚመለከት በመሆኑ ድጋፌን ለመግለጽ ወጥቺያለሁ" ሲሉ ገልጿል። ወጣት መሰለ እቁባይ በበኩሉ ስለ ሰላም እየዘመሩ የትግራይ ህዝብን ሰላም ለማወክ መሞከር አግባብ ያልሆነና ተቀባይነት እንደሌለው ተናግሯል። የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ሆኖ የታገለው ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በመሆኑ ማንኛውንም ጭቆና እንደማይሸከም አመልክቷል። በሰልፉ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማው እንዳሉት ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲከበር የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር በመሆን መስዋዕት ከፍሏል። በአሁኑ ወቅትም ከሌሎች ሰላም ወዳድ የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆን ህግ ለማስከበር ድምጹን በሰላማዊ መንገድ እያሰማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "በዞናችን የማንነት ጥያቄ ባይኖርም አንዳንድ ሰላም የማይፈልጉ አካላት ሰላሙን ለመንሳት ሌት ተቀን ቢሰሩም ህዝቡ በትዕግስት እና በሰላም ድምጹን እያሰማ ነው" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም