ሰልጥነው የስራ እድልና መጠለያ ባለመመቻቸቱ መቸገራቸውን ወጣቶች ተናገሩ

80
ሐረር ህዳር 15/2011 የስራ እድልና መጠለያ ባለመመቻቸቱ ወደ ቀድሞ ህይወታችን ለመመለስ እየተገደዱ መሆናቸውን ከሐረር በመሄድ በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል ሰልጥነው የተመረቁ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ተናገሩ። በሐረር ከተማ ቀበሌ 17 በተለምዶ አራተኛ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ለአስራ አንድ ወር የተሰጠውን ስልጠና አጠናቆ በሎደር ኦፕሬተር የተመረቀው ወጣት ሲሳይ ነጋሽ አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ እንዳለው ከስልጠናው በኋላ በአፋር ክልል  መሬት ተሰጥቷቸው በእርሻ ስራ እንዲሰማሩ ቢደረግም አዋጭ ባለመሆኑ ትተውት ወደነበሩበት ሐረር ተመልሰዋል። " ስምንት ዓመታትን በጎዳና ህይወት አሳልፌያለው፤  ለመለወጥ አስቤ ስልጠና ወስጄ ወደ ስራ ለመሰማራት ብፈልግም  የመጠለያና የስራ እድል በማጣቴ ወደ ቀድሞ ህይወቴ ለመመለስ እየተገደድኩ ነው፤  የክልሉ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጠን እንፈልጋለን" ብሏል፡፡ ሌላው ወጣት ቢኒያም ጌታቸው  "መንግስት እራሳቸውን ይለውጣሉ ብሎ ስልጠናውን እንደዘረጋልን ሁሉ የክልሉ ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤትም የስራ እድልና መጠለያ ችግራችንን ይፍታልን " ብሏል፡፡ "ቤተሰብ ስለሌለኝ መንግስትን የምጠይቀው ነገር የማረፍያ ቦታ ነው " ያለችው በኤሌትሪክ ሙያ የሰለጠነችው ወጣት እናትዓለም ተገኝ ናት፡፡ ወደ ጎዳና ተዳዳሪ ህይወት እንዳትመለስ ትኩረት ሊሰጣት እንደሚገባ የተናገረች ወጣቷ በተለይ  የብድር አገልግሎት ከተመቻቸላትም  በሰለጠነችበት ሙያ  ተደራጅታ እራሷን ለመቻል ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች። ከማዕከሉ ሲወጡ ክልሉ ሁሉን ነገር እንደሚያመቻችላቸወ የተነጋራቸው ቢሆንም ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ሆኖ እንዳላገኙት የተናገረው ደግሞ በብረታ ብረት ሙያ የሰለጠነው ወጣት አብዲ አደም ነው። " መንግስት ችግራችንን ተረድቶ መፍትሄ ይስጠን"  ብሏል። የሐረሪ ክልል የማህበራዊ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በብረታብረት ኢንጅነሪንግ የአዲስ ራዕይ ማሰልጠኛ ማዕከል ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ከ500 በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በተለያዩ ሙያ መሰልጠናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰልጥነው  አምራች ዜጋ እንዲሆኑና  ህይወታቸውንም  እንዲቀይሩ መደረጉን አመልክተዋል። ኃላፊው እንዳሉት በሶስተኛው ዙር ከክልሉ ከሔዱት መካከል  61 ወጣቶች ስልጠና መጨረሳቸውና  በክልሉ ስራ ይሰጠን ብለው ከ15 ቀናት በፊት ባቀረቡት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በጥያቄው መሰረት ውይይት አካሄደው የምግብ ጥያቄያቸው መመለሱን ጠቁመው የመጠለያ እና የስራ እድል እንዲያገኙም  ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ መሆኑንና በአጭር ጊዜ መፍትሄ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል። የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ጀማል መሀመድ በበኩላቸው ወጣቶቹ ወደ ተቋሙ መጥተው ያቀረቡት ጥያቄ እንደሌላ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም እንደ ሌሎች ወጣቶቹ ጥያቄ ካቀረቡ ተቋሙ በማህበር የማደራጀት እና ብድርም እንዲመቻችላቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም