ከሻሸመኔ ወደ አዲስ አበባ በሕገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 55 ኩንታል ቡና ተያዘ

59
አዳማ ህዳር 15/2011 ከሻሸመኔ ወደ አዲስ አበባ በሕገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 55 ኩንታል ቡና ትናንት መያዙን ፖሊስ ገለጸ። የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንዳስታወቁት ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የተያዘው ቡና ከ300 ሺህ ብር በላይ ግምት አለው። ኮድ 3 አዲስ አበባ 36952 በሆነ የጭነት ተሽከርካሪ የተያዘው በአዳሚቱሉ ወረዳ ቆሬ አዲ ቀበሌ ሲደርስ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ መሆኑንም  አስረድተዋል። የተሽከርካሪው ሹፌርና ረዳቱ ለጊዜው ቢሰወሩም፣ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ በክትትል ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል። ሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ በአገር ኢኮኖሚ ላይ በተለይ ቡና  የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በመሆኑ ጉዳቱ የከፋ መሆኑ ኅብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመተባበር  ድርጊቱን እንዲገታው አሳስበዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም