ማዕከሉ ሁለት ምርጥ የሽምብራ ዝሪያዎች ወደ አርሶ አደሩ ለማስፋት እየሰራ ነው

76
አክሱም ህዳር 15/2011 በምርምር የወጡ ሁለት ምርጥ የሽምብራ ዝሪያዎች ወደ አርሶ አደሩ ማሳ ለማስፋት እየሰራ መሆኑን በትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአክሱም ግብርና ምርምር ማዕከል ገለጸ። ዲምቱና ዳሎታ የተባሉ ምርጥ የሽምብራ ዝሪያዎች የአክሱምና ደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከላት በጋራ ያወጧቸው  ናቸው። ማዕከሉ ዝሪያውን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ በትግራይ ማእከላዊ ዞን ታህታይ ማይጨው ወረዳ የአንድ ቀን የመስክ ጉብኝት ተካሄዷል። የትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አባዲ ግርማይ በዚህ ወቅት እንዳሉት  በምርምር የተገኙት ምርጥ የሽምብራ ዝሪያዎች አስፋፍተው ምርታማነት በማሳደግ ወደ ውጭ ለመላክ  እንዲቻል እየተሰራ ነው። በተለይ በክልሉ ማዕከላዊ እና ሰሜናዊ ምዕራብ ዞኖች የሽምብራ ምርታማነት ለማሳደግ ተስማሚ ምህዳር መኖሩን በምርምር እንደተረጋገጠ አስታውቀዋል። ዝሪያውን በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ እድሉ መኖሩን ገልጸው ግብርናን ለማዘመን  የምርምር ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ዶክተር አባዲ እንዳመለከቱት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ለማሻሻል በየደረጃው ያለ አመራር በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል። አሁን የተገኘውን ተሞክሮ ወደ ሌላ አካባቢ በመውሰድ ተግባራዊ ለማድረግ ማህበራትና ሞዴል አርሶ አደሮች በማሳተፍ ሊሰራበት ይገባል፡፡ በአክሱም እርሻ ምርምር ማዕከል የስነ አዝርእት ተማራማሪ አቶ ኪሮስ ወልዳይ በበኩላቸው ማዕከሉ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በምርምር ያገኛቸውን የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማስተዋወቅ ሰራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። "የሽምብራ ምርጥ ዘር ለማገኘት በአምስት ዓይነት የሰብል ሙከራ ተደርጎ ሁለቱ በምርታማነታቸው የተሻለ ሆነው በመገኘታቸው በአርሶ አደሮች ተመርጠዋል" ብለዋል። አሁን በምርምር የተገኙት ዲምቱና ዳሎታ ምርጥ ዘር ድርቅ እና በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ ሆነው እንዳገኙት አቶ ኪሮስ ገልጸዋል። አርሶ አደሩ በተለምዶ ከሚዘራቸው ሽምብራ በሄክታር ከ15 ኩንታል በታች ምርት እንደሚያገኝ ጠቁመው በምርምር የወጡ ሁለቱ ዝሪያዎች በሄክታር ከ26 ኩንታል በላይ እንደሚሰጡ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ መረጋገጡን አመልክተዋል። በዚህም ዲምቱና ዳሎታ በአርሶ አደሩ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘታቸው  ወደ ሁሉም አከባቢዎች ለማስፋፋት እየተሰራ ነው። "ሽምበራ በገበያ ላይ አዋጪ በመሆኑ  አርሶ አደሩ ይህንን አማራጭ ወስዶ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው  ከፍ ለማድረግ ይቻላል" ብለዋል። በታሕታይ ማይጨው ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አብርሃ ተወለደብርሃን በሰጡት አስተያየት ያገኙትን  ምርጥ ዘር ተጠቅመው ግማሽ ሄክታር መሬት እንዳለሙ ተናግረዋል። ከቡቃያ ጀምሮ እስከ ፍሬ አያያዙ ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ እና በተለምዶ ከሚዘራ የሽምብራ ዝርያ የተሻለ መሆኑን ተሞክራቸው አካፍለዋል። የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ሰብሉን በማየት በሚቀጥለው የመኸር ወቅት ለመዝራት ጉጉት እንዳደረባቸው ጠቁመዋል። በውስን አርሶ አደሮች የተካሄደው የምርምር ስራ በቀጣይ ዝሪያውን ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ  የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ገብረህይወት ብርሃነ ናቸው። "ብዙ ምርት ሊሰጥ እንደሚችል ከተሞክሮ አይተናል፤ በቀጣይ እኛ እጅ ገብቶ አበዝተን እርሶ አደሩን እንዲጠቀምበት እንሰራለን" ብለዋል። በአክሱም የምዕባለ ምርጥ ዘር ማባዛት እና የገበያ ማህበር የምርጥ ዘር ብዜት ባለሙያ ገብረመስቀል ግደይ በበኩላቸው በምርምር የተገኙ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ተቀብለው በማባዛት ለሞዴል ለአርሶ አደሮች በማከፋፈል የምርጥ ዘር እጥረት  ለማቃለል እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም