የስነ-ህዝብ ፖሊሲ ሊሻሻል ነው

189
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 ለ25 ዓመታት ስራ ላይ የቆየው የስነ-ህዝብ ፖሊሲ ያመጣው ለውጥ በጥናት ተፈትሾ እንደሚሻሻል የፕላን ልማት ኮሚሽን አስታወቀ። በኮሚሽኑ የስነ-ህዝብና ልማት አስተባባሪ አቶ ፍቅሬ ገሶ ለኢዜአ እንዳሉት በ1985 ዓ.ም ፀድቆ ስራ ላይ የዋለው የስነ-ህዝብ ፖሊሲ አሁን ካለው የህዝብ እድገትና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አንፃር ተሻሽሎ መውጣት ይገባዋል። ፖሊሲው በዚያን ወቅት በኢትዮጵያ ታይተው የነበሩ ዘርፈ-ብዙ ችግሮችን እንዲፈታ ታስቦ ስራ ላይ የዋለ መሆኑንም አስታውቀዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በፖሊሲው ሊመለሱ የታሰቡ ስትራቴጂያዊ እቅዶች ተቀርፀው ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየታቸውን አቶ ፍቅሬ ገልፀዋል። በፖሊሲው ከተካተቱ መካከል በወቅቱ የህዝብ ቁጥርን ለማስተካከል የሴቶችን የጋብቻ እድሜ ወደ 18 ማሳደግ አንዱ ነው። በሌላ በኩል የህዝብ ቁጥሩን በየክልሉ ከማመጣጠን አንፃር በየክሊኒኮች የፅንስ መከላከያ እደላዎችን የማስፋፋት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። በስራ አጥነት የታየውን ቀውስ ለማስተካከልም በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወጣቶችና ሴቶች እንዲሳተፉ የማድረግ ስራ መሰራቱን አመልክተዋል። የገጠሩን ህብረተሰብ ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ እንዲሳተፍ ማድረግም በስነ-ህዝብ ፖሊሲው ከተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ነው። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩና የኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረታዊ ፍላጎቶችን በበቂ ሁኔታ በመመለስ በቀጣይ ለውጥ ከማምጣት አንጻር ፖሊሲው ክፍተት እንዳለበት ያሳያል ብለዋል። በሌላ በኩል በወቅቱ በነበረው የወጣት ቁጥር የተቃኘው የስነ-ህዝብ ፖሊሲ አሁን ካለው አብዛኛው ወጣት አንፃር በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ነው ያሉት።  በዚህና መሰል ምክንያቶች ሳቢያ የፖሊሲው አሉታዊ ጎን እየታየ መሆኑን ገልፀዋል።  ከዚህ በተጨማሪ የስራ አጥነትና ማህበራዊ አገልግሎቶች እጥረትን ለማሟላት አለማስቻሉን ገልጸዋል። በፕላን ኮሚሽንም ሆነ በመንግስት በኩል ፖሊሲውን ከማሻሻል አስቀድሞ ፖሊሲው ያመጣውን በጎና ደካማ ጎን ማየት አስፈላጊ መሆኑ በፕላን ኮሚሽንም ሆነ በመንግስት በኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቁመዋል። ፖሊሲውን ለመከለስ ከሚደረግ ጥናት የሚገኙ ግብአቶችን መሰረት በማድረግ በፖሊሲው ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግም ነው ያስታወቁት።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም