የወላድ እናቶች ማቆያ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር አደርጎታል

1120

አምቦ ህዳር 15/2011 በምዕራብ ሸዋ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በየጤና ጣቢያው እየተቋቋሙ ያሉት የወላድ እናቶች ማቆያ ማዕከላት በባለሙያዎች እገዛ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የእናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቶሌራ ጋሮማ እንዳሉት በዞኑ ባሉት 91 ጤና ጣቢያዎችና 7 ሆስፒታሎች የወላድ እናቶች ማቆያ ማዕከላት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተዘጋጅቷል፡፡

በሁሉም የጤና ተቋማት የማቆያ ማዕከላትን ከማዘጋጀቱ በተጓዳኝ አስፈላጊ ቁሳቁስ የማሟላትና የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፉት  አራት ወራትም ከ11 ሺህ በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ባለሙያዎች ታግዘው በጤና ተቋም እንዲወልዱ ማዕከላቱ መነሳሳት መፍጠራቸውን  ገልጸዋል፡፡

በነዚሁ ወራት ውስጥ ከ16 ሺህ ከሚበልጡ እናቶች ጋር ምክክር መደረጉን የገለጹት አስተባባሪው “ተሣታፊዎቹ  በአካባቢያቸው የሚገኙ ነፍሰ ጡር እናቶች  በጤና ተቋማት እንዲወልዱ በመቀስቀስና በማስተማር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል።

እስካሁን ባለው እንቅስቃሴም በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ሽፋን ከነበረበት ከ66  ወደ 69 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል።

ወይዘሮ አለምሸት ተካልኝ የአምቦ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ለመውለድ ሶስት ቀናት  ሲቀራቸው ወደ ጤና ተቋም ሄደው በወላድ እናቶች ማቆያ ውስጥ ማረፋቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በማቆያው ሆነው በጤና ባለሙያዎች በየጊዜው የጤና ክትትል ተደርጎላቸው ጤነኛ ልጅ መገላገላቸውንና እሳቸውም  በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ እንደረዳቸው ገልጸዋል።

ሌሎች እናቶችም በቤት ውስጥ ወልደው ለተለያዩ የጤና እክል ከሚዳረጉ ወደ ጤና ተቋም ሄደው መውለድ እንደሚኖርባቸው ከራሳቸው ልምድ በመነሳት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በቤት ውስጥ ሲወለድ በህጻኑም ሆነ በእናት ላይ የሚደርስ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ወደ ጤና ተቋም መጥተው መውለዳቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ታደለች ፈይሣ ናቸው፡፡

ወደ አዋሮ ጤና ጣቢያ የእናቶች ማቆያ ከመጡበት ዕለት ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች በቅርበት ክትትልና ክብካቤ  እንዳደረጉላቸውም ተናግረዋል፡፡

በእናቶች ማቆያው የተሟላ አገልግሎት እንደተሰጣቸው የገለጹት ወይዘሮዋ በአካባቢያቸው በርካታ እናቶች በቤት ውስጥ የሚወልዱ በመኖራቸው ከዚህ ታቅበው ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኤጀርሣ ለፎ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ መሠረት መስቀሉ በበኩላቸው “ወላድ እናቶች ቤት ውስጥ በልምድ አዋላጅ ከሚወልዱ ወደ ጤና ተቋም መጥተው በሰለጠኑ ባለሙያዎች ታግዘው መውለድን ልምዳቸው ሊያደርጉት ይገባል ” ብለዋል፡፡

በጤና ተቋም የመጀመሪያ ልጃቸውን እንደወለዱ ገልጸው ወደ ጤና ተቋም ከመጡበት ጊዜ አንስቶ የተደረገላቸው ክትትልና እንክብካቤ ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል።