የወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ሹመት በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እይታ

1936

ኢዜአ ሞኒተሪንግ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በየሳምንቱ በሚወስኗቸው አዳዲስ የለውጥ ውሳኔዎች ሳቢያ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ መገናኛ ብዙሃን የሁልጊዜ አብይ ዜና የይዘት አካል መሆን ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየወሰዷቸው የሚገኙ ለውጥ አምጪ ውሳኔዎችን ተከትለው መገናኛ ብዙሃኑ የተለያዩ ዘገባዎችን ያሰራጫሉ። በዚህ ሰሞን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው የሚነሱበት ጉዳይ አላጡም። ይህም ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሃላፊን የመሾማቸው ነገር በመገናኛ ብዙሃኑ እይታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን የቦርዱ ሃላፊ አድርገው በምክር ቤት እንዲሾሙ ማድረጋቸው በተለይ የውጭ መገናኛ ብዙሃኑ በሳምንቱ ካገኟቸው ጮማ ዜናዎች በአበይትነት ሊጠቀስ ይችላል።

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ ‘Former Opposition Leader’ የሚለውን ሃረግ እየደጋገሙ ከዚህ ቀደም ግለሰቧ የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት አባል እንደነበሩ በማንሳት ዘገባዎቻቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ። መገናኛ ብዙሃኑ ሃሳቡን የደጋገሙበት ምክንያትም ካሁን በፊት በነበሩት መንግስታት አይደለም ከተፎካካሪ ፓርቲ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የተለየ ሃሳብ ያለው ግለሰብን ለሃላፊነት የማጨት ታሪክ ተከውኖ ካለማወቁ ጋር የነበረውን ሁኔታ ለማሳየት ነው። በሌላም በኩል ግለሰቧን በስም እየጠሩ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ሆኑ በማለት ‘እኛም በደንብ እናውቃታለን’ ያስባለ ዘገባዎቻቸውን ለታዳሚዎቻቸው አሰራጭተዋል።

በተለይ በሁለተኛው ሃሳብ ላይ ከተነሳው ጋር በተያያዘ ዘገባውን ያሰራጨው ቢቢሲ  ነው፡፡ ‘Ethiopian’s Birtukan Midksa appointed election boss’ ሲል ነው የዜና ማሰራጫው ዘገባውን ያደረሰው። ቢቢሲ ሲቀጥልም በቅርቡ ለሴቶች ከተሰጡ ሃላፊነቶች ቁልፍ የሚባለው ለወ/ሪት ብርቱካን እንደተሰጠ ከጠቀሰ በኋላ ግለሰቧ በስደት ሰባት አመታትን በውጪ እንዳሳለፉ ጠቁሟል።

የሬውተርስ የዜና ወኪል በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለተመራጯ የሰጡትን ምስክርነት አካቶ አቅርቧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሃላፊነቱን ለወ/ሪት ብርቱካን የሰጠበት ምክንያት ግለሰቧ ህገ መንግስቱንም ሆነ ሌሎች የሃገሪቷን ህጎች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እንደሆነ የተናገሩትን በዜና ዘገባው አካቷል።

የቀድሞ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ሆኑ ሲል የዘገበው ዴይሊ ሜይል ሃለፊነቱ እኤአ በ2020 ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እንዳሳቡ ማሳያ ነው ሲል አክሏል። ወ/ሪት ብርቱካን እንዲመሩት የተሾሙበት ምርጫ ቦርድ እኤአ በ2015 ገዥው ፓርቲ ሁሉንም የምክር ቤት ወንበሮች እንዳሸነፈ ይፋ አድርጎ እንደነበርም የዜና ምንጩ አስታውሷል።

ሹመቱን ተከትሎ የወጣው የአለም አቀፉ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም (የሂውማን ራይትስ ዎች) መግለጫ ኢትዮዽያ የምርጫ ቦርድ ተቋሟን ነፃ እያደረገች እንደሆነ አመልክቷል። ከወደ ኢትዮዽያ መልካም ዜና እንደተሰማ ያስቀመጠው መግለጫው ከዚህ ቀደም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪ እንዲሁም የፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩትን ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ሃገሪቷ ለምርጫ ቦርድ በሃላፊነት መሾሟን አወድሷል። ከዚህ ቀደም ዝግ ሆኖ የቆየውን የሃገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር መንግስት የተለያዩ የለውጥ እርምጃዎች እየወሰደ በማሻሻል ላይ እንደሚገኝም አለም አቀፉ ተቋም በመግለጫው አሳይቷል።

ልክ እንደሌሎቹ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ኤ ኤፍ ፒም ‘የቀድሞዋ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪ’ የሚለውን ሃረግ በማስቀደም ዘገባውን ያሰራጨ ሲሆን ግለሰቧ እኤአ በ2005 በሃገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ወቅት ባንፀባረቁት አቋም ለዕውቅና ሊበቁ እንደቻሉም አስከትሏል። በወቅቱም ከተፈጠረ ሁከት ጋር በተያያዘ ወ/ሪትዋ ለእስር መብቃታቸውንም ኤ ኤፍ ፒ አልዘነጋውም። አሁን ያገኙት ሃላፊነት ከዚህ ቀደም በከፍተኛው ፍርድ ቤት በዳኝነት ሲከውኑት ከነበረው እምብዛም የተለየ እንዳልሆነ የተናገሩትን ሃሳብም የዜና ዘገባው አካቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እኤአ በ2020 የሚካሄደውን ምርጫ ነፃና ተአማኒ ለማድረግ የሚያስችል ሹመት ሰጡ በሚል ዘገባውን የጀመረው ገልፍ ቱ ዴይ የቀድሞዋ የሚለውን ቃል አስቀድሞ ወ/ሪት ብርቱካን ምርጫ ቦርድን ለመምራት ሃላፊነት እንደተሰጣት አስቀምጧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምርጫ ማሸነፍ ይልቅ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ማካሄድን ማስቀደም እንደሚገባ ያስተላለፉትን መልዕክት ገልፍ ቱ ዴይ የዘገባው ማጣፈጫ አድርጎ አቅርቦታል።

አልጀዚራ ‘የቀድሞዋ የፍርድ ቤት ዳኛ’ ሲል ዘገባውን ጀምሮ ከፍተኛውን የመንግስት ስልጣን ተቀዳጁ ሲል ደግሞ አስከትሏል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ አገዛዝ ዘመን 50 በመቶው የካቢኔ ቦታ ከያዙት ሴቶች በተጨማሪ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሄር ቦታ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቱ ሃላፊነት በሴቶች እየተመራ እንደሚገኝም አልጀዚራ አፅንኦት ሰጥቶታል። እንደ አልጀዚራ የሃገሪቱን የምርጫ ቦርድ ለመምራት ደግሞ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሃላፊነት ተጠቁመው በምክር ቤቱ ይሁንታን አግኝተዋል።

በርካታ የአህጉሪቱ እንዲሁም ሌሎች ክፍለ አለማት የዜና አውታሮች ለጉዳዩ የተለየ ስፍራን በመቸር መረጃዎቻቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ። በሃገሪቱ ታሪክ ታስበው የማይታወቁ ውሳኔዎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየወሰኑ ለውጡን እውን ለማድረግ እየተጓዙበት ያለውን መንገድ አድንቀው ለመጨረስ ፋታ ያጡት መገናኛ ብዙሃኑ ዛሬ ያገኙትን ዘገባ በፍጥነት እያሰራጩ ነገስ ምን አዲስ ነገር ከሃገሪቷ እንሰማ ይሆን እያሉ በጉጉት ሲጠባበቁ ማየቱ ተለምዷል። ለጊዜው እሰካሁን በተከወኑት የለውጥ እርምጃዎች ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ ከላይ የቀረበውንም ጉዳይ ከግምት ያስገባ የተለያዩ ዘገባዎቻቸውን እያሰራጩ ለነገ መረጃዎቻቸው ብዕሮቻቸውን አሹለው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።