የኦዲት ክፍተቶቻቸውን የማያሻሽሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ተባለ

78
አዲስ አበባ ህዳር 14/2011 የኦዲት ክፍተቶቻቸውን የማያሻሽሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በህግ ተጠያቂ  ሊሆኑ እንደሚገባ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ። ተቋማቱ በየዓመቱ የኦዲት ክፍተቶችን እያሳዩ ያለ ሲሆን በወቅቱ እርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጿል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታየውን የኦዲት ግኝት ችግሮች ለመፍታት ከሁለት ዓመት በፊት ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ኮሚሽን እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴርና የፌዴራል ዋና ኦዲተር ኮሚቴውን በዋናነት የሚመሩ ነበሩ። የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የሚታዩ የኦዲት ግኝት ችግሮች ጥልቀት ያላቸው በመሆኑ በቀላሉ ሊፈቱ አልቻሉም። የከፍተኛ ትምህርት አዋጅና የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ የተጣጣመ ባለመሆኑም በኦዲት ግኝት ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲባባሱ ማድረጉን ተናግረዋል። የከፍተኛ ትምህርት የማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ዩኒቨርሲቲዎች የውስጥ ገቢ ለማመንጨት ኢንተርፕራይዝ ማቋቋም እንደሚችሉ የተደነገገ ሲሆን ኢንተርፕራይዞቹ እንዴት ይቋቋሟሉ? በማን ካፒታል? የኢንተርፕራይዞቹ ባለቤት ማነው? የሚሉት በአዋጁ ላይ በግልጽ እንዳልሰፈረ አቶ ገመቹ አብራርተዋል። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ፕሬዝዳንቶችን የኢንተርፕራይዙ ባለቤት በማድረግ ህገወጥ ተግባር እንዲፈጽሙ እያደረጉ መሆኑንም አመልክተዋል። ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ የሚፈጸሙ ክፍያዎች፣ የግዢ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተሉ ግዢዎችና የገቢ አሰባሰብ ክፍተቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮች እንደሆኑም አቶ ገመቹ አስረድተዋል። ለአብነትም በ2007 በጀት ዓመት የሐሮማያ፣ የደብረማርቆስ፣ የባህርዳር፣ የሀዋሳ፣ የዲላና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ  ክፍያ ፈጽመው የተገኙ ተቋማት እንደሆኑም ገልጸዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ውስጥ በኦዲት የተገኘው ችግር እንዲፈታ በወቅቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተለያዩ ጥረቶች እንደተደረጉ የገለጹት ዋና ኦዲተሩ አጥጋቢ ውጤት ባለመገኘቱ ህግና ስርዓት የሚጥሱ ተቋማት በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም ይናገራሉ። ከግዢና ከሌሎች ክፍያዎች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችም በአብዛኛው ያልተፈቱ ችግሮች ሲሆኑ ጥቂቶች ግን መሻሻል ማሳየታቸውን ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል። በ2008 በጀት ዓመት ደግሞ የጅማ፣ የደብረታቦር፣ የደብረብርሃን፣ የአዲስ አበባ፣ የወላይታ ሶዶ፣ የዲላ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ ክፍያ የፈጸሙ ተቋማት እንደሆኑም አቶ ገመቹ ገልጸዋል። በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኦዲት ግኝት ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ የክፍያ ተመን በየዓመቱ እልባት ያልተገኘለት አንዱ ችግር እንደሆነም ተናግረዋል። በ2009 በጀት ዓመት በተመሳሳይ የአዲስ አበባ፣ የዲላና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ ያለአግባብ ክፍያ የፈጸሙ ተቋማት እንደሆኑም ገልጸዋል። በሚመለከታቸው አካላት ሳይፈቀድ የትርፍ ሰዓት ክፍያ መፈጸም፣ ለሰራተኞች አበል፣ ማበረታቻ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ ክፍያ መፈጸም፣ ሰራተኞች መስክ ሳይወጡ የውሎ አባል መክፈል፣ ተቋሙን የለቀቁና ለትምህርት ውጭ አገር ሄደው በዚያው ለቀሩ ሰራተኞች ለበርካታ ወራት የደመወዝ ክፍያ መፈጸም በተጨማሪነት በኦዲት ግኝት የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮች እንደሆኑም አቶ ገመቹ አብራርተዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱሉ እንዳሉት ዋና ኦዲተር በየጊዜው የሚያወጣቸው የኦዲት ሪፖርቶች ለተቋሙ የምርመራ ሥራ ግብዓት ነው። ዋና ኦዲተር የሚያወጣቸው በተለይ የህዝብና የመንግስት ሀብት ምዝበራ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ወንጀሎችን እየተከታተለ እንዲታረሙ እያደረገ ቢሆንም በቀጣይ የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ የህግ ተጠያቂነቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2008 በጀት ዓመትን የኦዲት ሪፖርት ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ "በተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ችግርን ማሻሻል ያልቻሉ ተቋማት በፍትሐ ብሄር ህግ እንዲጠየቁ ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለምርመራ በመላክ የምርመራው ውጤቱም ለምክር ቤቱ ሪፖርት የሚሆንበት የተጠያቂነት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል" ማለታቸው ይታወሳል። ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ለምክር ቤቱ ሲቀርቡ በነበሩ የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች ሳይጠቀሱ የማይታለፉ እውነታዎች ሲሆኑ በርካታ ተቋማት አሁንም የመንግስት ሀብትን ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ መጠቀማቸውን ገፍተውበታል፡፡ ከዓመት ዓመት ከፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት ስማቸው ሳይጠቀስ ከማያልፉ ተቋማት መካከል ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም