በዞኑ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጋ ወቅት የወጣቶች በጎ ፈቃድ ሥራ ተጀመረ

49
አምቦ ህዳር 14/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጋ ወቅት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ መጀመሩን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 340 ሺህ ወጣቶች ከተያዘው ህዳር ወር መግቢያ ጀምሮ የእውቀትና የጉልበት አስተዋፅኦ በማድረግ በመሳተፍ ላይ ናቸው። የምዕራብ ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሶምሳ እንደገለጹት በዞኑ 22 ወረዳዎች እየተከናወነ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ከሆኑ የዞኑ ወጣቶች መካከል ግማሾቹ ሴቶች ናቸው። በየዓመቱ በክረምትና በበጋ ወቅት በወጣቶች በሚሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ከሚሰጡት አገልግሎቶች መካከል ትምህርት፣ የደም ልገሳና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። አረጋዊያንን መርዳት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ግንዛቤ መስጠት፣ በአገር ሰላምና አንድነት ላይ ውይይት ማካሄድ ወጣቶቹ ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከልም ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ የአቅመ ደካሞችን የደረሰ ሰብል የመሰብሰብ ሥራን ጨምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው 18 የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ለ720 ሺህ ሰዎች አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ መያዙን ነው ያስረዱት፡፡ አቶ ተስፋዬ እንዳሉት በበጋው ወራት የሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የትምህርት ጊዜን በማይሻማ መልኩ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም ከትምህርት ሰዓት ውጪ ነው። የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወጣት ፍሮምሳ ንጋቱ በሰጠው አስተያየት ባለፈው ክረምት ደም በመለገስ፣ አረጋዊያንን በማገዝ፣ አካባቢን በማጽዳትና በመሳሰሉት የበጎ አገልግሎት ተግባራት በመሳተፍ ሕብረተሰቡን ማገልገሉንና በእዚህም የህሊና እርካታ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡ በበጋ ወራትም በተለይ የሰው ሕይወት ለማዳን ደም በመለገስና አቅመ ደካሞችን በመርዳት የበጎ ፈቃድ ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል። ባለፈው ዓመት የከተማ ውበትን በመጠበቅ ሥራና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር መሳተፏን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ሃዊ ኦላና ናት። በበጋ ወራትም በተለይ የእናቶችን ሕይወት ለመታደግ ደም ከመለገስ ባለፈ አቅመ ደካሞችን በመርዳት የበጎ ፈቃድ ሥራዋን አጠናክራ ለመቀጠል ወደተግባራዊ ሥራ መግባቷን ተናግራለች። ባለፈው የክረምት ወራት በዞኑ 22ት ወረዳዎች 240 ሺህ 915 ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የተሳተፉ ሲሆን በእዚህም 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን  ብር የሚገመት አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም