በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ ይሆናሉ

60
አዲስ አበባ ህዳር 14/2011 በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ አመዝኖባቸው እንደሚቆዩ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። የአየር ሁኔታው የመኸር ሰብል ለሚሰበስቡ አካባቢዎች ጠቀሜታው ከፍ ያለ በመሆኑ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ብሏል። በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው፣ በምስራቅና በደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ አልፎ አልፎ የሌሊትና የማለዳ ቅዝቃዜ እንደሚስተዋልም ኤጀንሲው ጠቁሟል። ቅዝቃዜው በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ውርጭ የሚያስከትልና ከሞላ ጎደል ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችልም ኤጀንሲው በትንበያው አመልክቷል። በደቡብና በደቡብ ምስራቅ እንዲሁም በመካከለኛው የአገሪቷ አካባቢዎች አነስተኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል ብሏል። የሚጠበቀው መጠነኛ እርጥበትም በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበጋ ወቅት ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች፣ እንዲሁም ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት ጥሩ እንደሆነም ትንበያው ያመለክታል። አየር ሁኔታው በአብዛኛው የመኸር ሰብል ለሚሰበስቡ አካባቢዎች ጥሩ ቢሆንም የሚጠበቀው አነስተኛ የዝናብ መጠን የምርት አሰባሰቡን ሊያስተጓጉል ስለሚችል አርሶ አደሩ ምርቱን ቀድሞ እንዲሰበስብ ኤጀንሲው በላከው መግለጫ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም