የከተማ ታክሲዎች ትርፍ መጫንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል መፍትሔ ያላገኘ ተግባር ሆኗል

1822

ህዳር 9/ 2011 በመዲናዋ የታክሲዎች ትርፍ መጫንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል እያስመረራቸው መሆኑን ያነጋገርናቸው የታክሲ ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

ተገልጋዮቹ እንደሚሉት ተግባሩ ህገወጥ መሆኑን ብያውቁም ከትራንስፖርት እጥረት የተነሳ ጠዋት ለስራ ለመድረስ ማታ ደግሞ የበለጠ ችግር እንዳይገጥማቸው የተጠየቀውን ብር መክፈልም ትርፍ ተጭነው ይሄዳሉ፡፡

ወጣት ጀማል በረካ ጠዋትና ማታ በትርፍ መጫንና ከታሪፍ በላይ በእጥፍ ከመክፈል ውጭ አማራጩ ጠባብ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በተለይ ምሽት የአንድ ብር ከሃምሳ ሳንትም መንገድ እስከ አምስት ብርና አስር ብር ከመክፈል በተጨማሪ ባለሁለት ሰው ወንበር ላይ ሶስት ሰው በመሆን እንደሚሳፈር ነው ወጣቱ የሚናገረው፡፡

ተጠቃሚዎች አካሄዱ ተገቢ እንዳልሆነ እያወቁም ያሰቡት ቦታ ለመድረስ ስባል ብቻ  የተጠየቀውን የማድረግ ልምድ በመዳበሩ ህገ ወጥ አሰራር ህጋዊ እየሆነ መምጣቱን የገለጸው ወጣቱ ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ ነው ይላል፡፡

ሌላው ተጠቃሚ አቶ ማስረሻ ተሾመ እንዳሉት “እኛ በታክሲ አገልግሎት ላይ የሚደርስብንን እንግልት ለመከላከል መብታችንን ሳናውቅ ቀርተን ሳይሆን ለከፋ ችግር እንዳንጋለጥ ከሩቅ መጥተን ጠዋት ለስራ ለመድረስና ማታም ቤታችን ለመግባት ስንል ነው” ይላሉ፡፡

ታክሲዎች በራሳቸው በሚያስከፍሉት ተመን እንጂ መንግስት ባወጣለቸው ታሪፍና ታፔላ አለመሥራታቸው የቁጥጥር ችግር መኖሩን ያሳያል ነው ያሉት፡፡

ለትራፊክ ደንብ ጥሰት በየአቅጣጫው የሰውን ፍሰት መሰረት ያላደረገና ያልተመጣጠነ ስምሪት ዋነኛ  መንስኤ መሆኑን የተናገሩት አቶ እሼቱ ወርቁ የሚመለከተው አካል  ጥናት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ መፍትሔ ልሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላው የታክሲ ተጠቃሚ አቶ ከምሶ ግራኝ በመንገድ ብልሽት ሰበብና በቁጥጥር ማነስ ምክንያት ታክሲዎች የመሐል ከተማ አጭር መንገዶችን አቆራርጠው መጫን እንጂ ወደ ጫፍ ወጥተው እንደማይሰሩ ተናግረው፤ “እየደረሰብን ያለው ችግር ከገንዘብም በላይ፤ ተሳፋሪን ተጠጋጋ ካልሆነ ውረድ ማለት ሰብዕናችንን የሚጎዳ ነው“ ይላሉ፡፡

የዛሬን ችግር አይተን መብታችንን ማስከበር እንዳንዘነጋ የተሳሳተውንም ማስተማር ይገባናል ያሉት አቶ ጣሰው ሞላ ተሳፋሪው በራሱ አንዱ መብቱን ስጠይቅ ሌላው የሚቃወም በመሆኑ  “ ችግር ፈጣሪም እኛው፤ ተጎጂም እኛው ነን” ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በአዲስ አበባ የታክሲ ትራንስፖርት አሰጣጥ ላይ በየጊዜው የሚታዩ የትርፍ መጫንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፤ አቆራርጦና በስምሪት ያለመሄድ ችግር መኖሩን ተናግረዋል፡፡

“ተጠቃሚው ወቅታዊ ችግሩ ላይ ማዘምበል እንጂ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገው ጥረት አናሳ በመሆኑ ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል” ያሉት ሃላፊው ለትራፊክ ፖሊስ ጥቆማ የሚሰጡ ሰዎች በጣም ጥቂት እንደሆኑ ነው የገለፁት፡፡

ትራፊክ ፖሊስ ጥቆማ ሲደርሰው ተካታትሎ እንርምጃ እንደሚወስድ የገለጹት ኮማንደር ፋሲካ  ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ላይ  የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በአገልግሎቱ ላይ የሚታየውን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሆነ  ጠቁመው ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ህብሰተሰቡ መብቱን ማስከበርና ህገወጥነትን በጋራ መከላከል ይገባዋልም ብለዋል ኮማንደር ፋሲካ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ክዳኔ በበኩላቸው  በህብረሰተሰቡ የተነሱ ችግሮች መኖራቸውን  አምነው የፌደራል የትራፊክ ደንብ ጥሰት የአዲስ አበባ ከተማን ያላገናዘበ ነው ይላሉ፡፡

ለዚህም ማሳያው ደንብ ተላልፈው ሲገኙ የተቀመጠው መቀጫ ከህጉ ጥሰት በታች/ተመጣጣኝ ያልሆነ በመሆኑ ችግሩን መቀነስ አልቻለም ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ሞሲሳ በሀገሪቱ የነበረው የትራፊክ ደንብ የከተማዋን ሁኔታ ያገናዘቤ አይደለም የተባለው እውነት መሆኑን ገልጸው እየታየ ያለውን ችግር በጥቂት ወራት ውስጥ ለመፍታት ከከተማው ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እንደምሰሩም ተናግረዋል፡፡