የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

3899

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ላላት ግንኙነት የሰጠችውን ትኩረት እንደሚያሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንዳሉት ፖል ካጋሜ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት ነው።

በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩና የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ሩዋንዳ ችግር ላይ በነበረችበት ወቅት ቀድማ በመድረስ አገሪቱ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንድትመለስ አስተዋጽኦ ማድረጓን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ ሁለቱ አገሮች ከስድስት ዓመት በፊት ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ስምምነት መፈራረማቸውንና ትብብሩን ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ማቋቋማቸውን ገልጸዋል።

ሩዋንዳ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ያጸደቀች ሲሆን ፍትሃዊ  የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ አቋም አላት።

የአፍሪካ ህብረት ማሻሻያ እንዲያካሂድና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲፈረም ሁለቱ አገሮች በጋራ መሰራታቸውም ተጠቅሷል።

ሩዋንዳ ከ40 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ ባለፈው ዓመት በሩዋንዳ ኤምባሲዋን ከፍታለች።