የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታችን ምርታማነትን ለማሳደግ መነቃቃት ፈጥሮልናል – አርሶ አደሮች

3936

ጊምቢ 24/2010 ህጋዊ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መያዛቸው የባለቤትነት መንፈሳቸው ጎልብቶ ለምርታማነት እድገት ጠንክረው በመስራት ላይ መሆናቸውን በምእራብ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶአደሮች ገለፁ ።

በዞኑ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የነጆና ጉሊሶ ወረዳ አርሶ አደሮች እንደገለፁት መሬታቸው በዘመናዊ መንገድ ተለክቶ ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲኖረው መደረጉ በራስ የመተማመን መንፈሳቸው በመፍጠሩ  መሬታቸውን በአግባቡ በማልማት  ምርታማነታቸውን  ማሳደግ ችለዋል ።

በነጆ ወረዳ የለሊሳ ዲላ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ፈቃዱ ኦላና በሰጡት አስተያየት ከአሁን በፊት በባህላዊ መንገድ በገመድ ተለክቶ የተሰጣቸው መሬት በወሰን መገፋፋት  ለግጭት መንስኤ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል ።

ባለፈው መጋቢት ወር መሬታቸውን በዘመናዊ ዘዴ በማስለካት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ባለቤት መሆናቸውን ከተረጋገጠ ወዲህ ግን በሰላምና በባለቤትነት መንፈስ በሙሉ አቅማቸው ለምርትና ምርታማነት ማደግ ትኩረት ሰጥተው ለመስራት እንዳነሳሳቸው አስረድተዋል ።

ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር አሰፋ ደምቢ በበኩላቸው  “በዘመናዊ ዘዴ መሬቴን በማስለካቴና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መያዜ  በመንግስት ዘንድ እውቅና ስለሚኖረኝ መሬቴን ከአደጋ መጠበቅና መንከባከብ እችላለሁ” ብለዋል።

”ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው መሬትን በዘላቂነት ለማልማት ፣ ለቤተሰብ አባል ለማውረስና አቅም በደከመ ጊዜ ለማኮናተር ጭምር ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ከስጋት ነፃ አድርጎኛል” ብለዋል ።

በጉሊሶ ወረዳ የሞጋ ኮበራ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር  አማኑኤል ነገራ እንዳሉት  ”የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታው የግብርና ልማቱን ለማስፋፋት አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ከእኛ የሚጠበቀው ጠንክሮ መስራት ብቻ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል ።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አፈወርቅ ደምሴ በዞኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአምስት ወረዳዎች ጂ ፒ ኤስ በተባለ ዘመናዊ መሳሪያ በመታገዝ የ11 ሺህ አርሶ አደሮች የእርሻ  መሬት ለመለካት ታቅዶ እንቅስቃሴ ተደርጓል ።

”ክንውኑ ከእቅዱ አንፃር ሲታይ ማሳካት የተቻለው 46 በመቶ ብቻ ነው” ያሉት ምክትል ኃላፊው ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አሁን ግን የሰው ሃይል በመጨመር በዞኑ በሚገኙ 12 ወረዳዎች ስራውን በተጠናከረ መንገድ በማከናወን እቅዱን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።