በሰላም አብሮ የመኖር ህልውናችንን የሚፈታተኑ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የኃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው-የሰላም ሚኒስትር

88
አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 በሰላም አብሮ የመኖር ህልውናችንን የሚፈታተኑ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የኃይማኖት ተቋማት ሚና  ከፍተኛ ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ። ሚኒስቴሩ ከፌዴራልና ከክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች ጋር ''የኃይማኖት አባቶች ለሰላም'' በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ  በአዲስ አበባ መክሯል። በመድረኩም ከሁሉም ክልሎችና ቤተ-እምነቶች የተወከሉ የኃይማኖት አባቶች በአሁኑ ወቅት እየተፈጠሩ ያሉትን የሰላም እጦቶች በፍጥነት ለመፍታት የኃይማኖት አባቶች ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተወያይተዋል። የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፣ "በሰላም አብሮ የመኖር ህልውናችንን የሚፈታተኑ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የኃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው"። በመሆኑም የኃይማኖት አባቶች የተለመደውን አስተምህሮትና ጥበባቸውን አክለው፣ የሰላም ጥሪ በኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጨፍ እንዲስተጋባ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። የኃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ለሰላም የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መስፈን የበለጠ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ አገረ ስብከት የኃይማኖት ተቋማት ምክትል ሰብሳቢ መጋቢ ስብሃት አለምነህ ጸጋው እንደገለጹት፣ ቤተክርስቲያን እስከ ዛሬም ስትሰራ የቆየችውና ተቀዳሚ ስራዋ ስለ ሰላም በመሆኑ  "አሁንም ይሄንኑ አጠናክረን እንሰራለን"። በአሁኑ ወቅትም ሰባቱም የእምነት ተቋማት አብረን እየሰራን የምንገኝ ሲሆን ግጭት በሚፈጠርበት ቦታ ሁሉ እየተገኘን እየተከላከልንና ወጣቱ በአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ እያስተማርን ነውም ብለዋል። የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ አደም አብዱልቃድር በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ አስከዛሬም ድረስ ችግሮቻችንን የምንፈታው በኃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች በመሆኑ "ይህ እሴታችን ዛሬም ያስፈልገናል" ብለዋል። ህዝቡ እንዲረጋጋና ወደ ቀደመው ሰላሙ እንዲመለስ በየቦታው እየዞርን የማረጋጋትና ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ከምን ጊዜውም በላይ እየሰራንበት ነው፣ ህብረተሰቡም ይሄንኑ በመረዳት የበኩሉን ማገዝ ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ ፈርሃ እግዚሃብሄር ያደረባት፣ ህዝቦችዋም ሰው አክባሪና የሚያስቀና እሴት ያላቸው  አገር በመሆንዋ ህዝቦቿ አሁንም የቀደመውን የአኗኗር ዘዬ በመከተል ለሌሎቹ ተምሳሌት መሆንን ልንቀጥልበት ይገባል ሲሉ የኃይማኖት አባቶቹ አክለዋል። ከተለያዩ የኃይማኖት ተቋማትና ከሁሉም ክልሎች የተሳተፉበት የምክክር መድረኩ ሁለት መቶ ያህል ተወካዮችን አሳትፏል። በጉባዔው ላይ "የአገር ሽምግልናና ሰላም፣ የእስልምና አስተምህሮና ሰላም እንዲሁም ሰላም በክርስትና አስተምህሮ" በሚሉ ርዕሶች ሶስት ጥናታዊ  ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተካሄደውባቸዋል። የሰላም ሚኒስትር ያዘጋጀው ይህ የምክክር መድረክ  በቀጣይም ለሶስት ወራት የሚቀጥል የንቅናቄ መድረክ የሚኖረው ሲሆን ከወጣቶች ጋር፣ ከሴቶች፣ ከህጻናት፣ ከኪነጥበብ ሰዎች፣ ከሚዲያ አካላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች እንደሚኖሩም ተገልጿል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም