የጀርመን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት ይፈልጋሉ - የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማህበር

55
አዲስ አበባ ህዳር 12/2011 የጀርመን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልጉ የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማህበር ዋና ዳይሬክተር ክርስቶፍ ካነንጌሰር ገለጹ። የኢትዮ - ጀርመን የንግድና ኢንቨስትመንት የጋራ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማህበር ዋና ዳይሬክተር ክርስቶፍ ካነንጌሰር እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ታላቅና ለኢንቨስትመንት ምቹ አገር ናት። የጀርመን ባለሃብቶችም ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እንደሃይል፣ ቴክኖሎጂና መድሃኒት ፋብሪካ ባሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሳተፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ባለሃብቶቹ ወደ ስራ ከመሰማራታቸው በፊት አገሪቷ ያላትን የኢንቨስትመንት ፖሊሲና የጸጥታ ሁኔታ በጥልቅ መፈተሽ እንደሚፈልጉም አውስተዋል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ  በበኩላቸው፤ ባለሃብቶቹ ወደ ኢንቨስትመንት ከመሰማራታቸው በፊት ለሚያደርጉት ዝግጅት ምክር ቤቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጀርመን ጉብኝት ካደረጉ በኋላ የአገሪቷ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ መነሳሳት እንዳሳዩ ጠቁመው፤መንግስት በቀጣይ የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም