ለደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የትሮይካ አባል አገራት ገለፁ

71
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ ቻይናና ጃፓንን በአባልነት ያቀፈው ትሮይካ ለደቡብ ሱዳን ስምምነት ድጋፉን እንደሚቀጥል ገለፀ። በተለይ በደቡብ ሱዳን የአሜሪካ፣ የእንግሊዝና የኖርዌይ ልዩ መልዕክተኞች በሰጡት መግለጫ የደቡብ ሱዳን ፓርቲዎች በጠላትነት መተያየት አቁመው ለአገር አንድነት መስራት እስኪጀምሩ ድረስ የሚሰጡትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። በደቡብ ሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ብሬይን ሹካር ፓርቲዎቹን ወደ ስምምነት ለማምጣት በህዝብ ተሰሚነት ባላቸው የደቡብ ሱዳን አብያተ-ቤተክርስቲያናት ምክር ቤት እና በሲቪል ማህበረሰብ አባላት በኩል መቅረብ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ እና የአውሮፓ ህብረት የደቡብ ሱዳን ፓርቲዎችን ለማስማማት ያደረጉት ጥረት ጠቃሚ መሆኑን መልዕክተኛው ጠቅሰው በዚህ ረገድ ትሮይካም የሚያቀርበውን ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል። በደቡብ ሱዳን የእንግሊዝ ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ክሪስቶፎር ትሮት በበኩላቸው "በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረሱ የተለያዩ ስምምነቶች በየጊዜው እንዳይጣሱ ለማድረግና በግጭት ምክንያትም የሚከሰተውን የዜጎች መፈናቀል ለማስቆም ያስችላል የሚባል ምክረ-ሀሳብ ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እናቀርባለን" ብለዋል። የተለያዩ አደራዳሪ አካላት የሚያቀርቡት የሰላም ሀሳብ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተቀባይነት እንዲኖረው ትሮይካ የደቡብ ሱዳናዊያንን ፍላጎት በማጥናት ምክረ-ሀሳብ እንደሚያቀርብ ገልፀዋል። የደቡብ ሱዳንና የጎረቤት አገራት መገናኛ ብዙሀን የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይሎች በሚመለከት የሚያሰራጯቸው ዘገባዎች ጥንቃቄ የታከለባቸው እንዲሆኑ ከተቋማቱ ጋር እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ሱዳን የኖርዌይ ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር እርሊንግ ስክጆንበርግ ናቸው። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ም ለዚህ ትኩረት እንዲሰጥ ሀሳብ አቅርበናል ነው ያሉት ልዩ-መልዕክተኛው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም