"ትውልድ አድን" የተሰኘ የህይወት ክህሎት ሥልጠና መርሃ-ግብር በዩኒቨርሲቲዎች ሊጀመር ነው

65
አዲስ አበባ  ህዳር 12/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢ ይፈጥራል ተብሎ የታመነበት "ትውልድ አድን" የተሰኘ የህይወት ክህሎት ሥልጠና መርሃ-ግብር ሊጀመር ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም ሠላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ዛሬ በዩኒቨርስቲዎች ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው  ይህንን የተናገሩት። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውም ሠላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር የሚያስችል "ትውልድ አድን" የተሰኘ የህይወት ክህሎት ሥልጠና መርሃ-ግብር ሊጀመር መሆኑን በዚህ ወቅት ጠቁመዋል። በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎችም መርሃ-ግብሩ በጅምር ላይ መሆኑን ጠቁመው በታዋቂ ግለሰቦች፣ በአርቲስቶችና በሥነ-ልቦና ባለሙያዎች የሚካሄድ ነው ብለዋል። ሚኒስትሯ እንዳሉት አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሥር-ነቀል የለውጥ ሂደት ላይ በመሆኗ የተለያዩ ችግሮችን እያስተናገደች ነው። በተለይም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሠሩ ኃይሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ማድረጋቸውን ጠቁመው ይህ እንዲሆን የተፈለገው ተቋማቱ "ትንሿን ኢትዮጵያ" የመወከል አቅም ስላላቸው ነው ብለዋል። ተማሪዎች ይህንን በመገንዘብ ችግሮችን ከወዲሁ መከላከል እንደሚገባ ገልጸው በዩኒቨርስቲዎች ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንዲጠናከር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም