በጥልቅ ተሃድሶው እየተመዘገቡ ያሉት መልካም ውጤቶችን ለማስቀጠል የአመራሩ ቁርጠኝነት ተጠየቀ

3624

መቱ ሚያዝያ 24/2010 በየደረጃው የሚገኝ አመራር በጥልቅ ተሀድሶ እየተመዘገቡ ያሉ መልካም ውጤቶችን በማስቀጠል ህብረተሰቡን በቅንነት ሊያገለግል እንደሚገባ የጨፌ ኦሮሚያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሰማን አባጎጃም አሳሰቡ፡፡

በኢሉአባቦር ዞን 13 ወረዳዎች ለሚገኙ የአመራር አካላት በጥልቅ ተሀድሶ ዙሪያ የሚሰጥ ስልጠናና ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚሁ ጊዜ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የጨፌ ኦሮሚያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰማን አባጎጃም እንዳስገነዘቡት  አመራሩ ተከታታይነት ባለው ጥልቅ ተሀድሶ በአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ አበረታች ውጤቶች በማስቀጠል ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጥልቅ ተሀድሶው እየተመዘገበ ያለው ውጤትና የመጣው ለውጥ ህዝቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላትና መዋቅሮች በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው ኦህዴድ ራሱን በጥልቀት በማደስና የተፈጠሩ ችግሮችን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለመቅረፍ ባደረገው ጥረት አበረታች ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 የስልጠና መድረኩ ዋና አላማም በጥልቅ ተሀድሶው እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማስቀጠል እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለው መዋቅር በትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሰራ ለማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጥልቅ ተሀድሶው አተገባበር ስልጠናው  ህብረተሰቡን በቅርበት ለሚያገለግሉት ለታችኛው የአመራር አካላት ተከታታይነት ባለው መልኩ እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

ከተናንት ጀምሮ ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት  በመቱ ከተማ እየተካሄደ ባለው የስልጠናና ግምገማ መድረክ ላይ ከዞኑ 13 ወረዳዎች የተወጣጡ ከ400 በላይ የአመራር አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡