በደብረ ብርሃን ከተማ በሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ሥራ ጀመሩ

129
ደብረ ብርሃን ህዳር 11/2011 በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ  በሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር  ወጪ የተገነቡ የልማት ሥራዎች ለአገልግሎት በቁ። በኅብረተሰቡ የጉልበት ተሳትፎ ጭምር ከተገነቡት መከከል የአራት ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ፣ አራት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ጥገናና ሁለት የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ይገኙባቸዋል። የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ብርሃን ገብረ ሕይወት እንደገለጹት ልማቱ የተካሄደው በከተማው ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለመሬታቸው የተሰጣቸውን የካሣ ክፍያ ለልማት እንዲውል በመፍቀዳቸው ነው። በዚህም የአካባቢው አርሶ አደሮች ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ የመጣውን ኢንዱስትሪ ልማት እንዳሳለጡት ተናግረዋል።አርሶ አደሮቹ ያበረከቱት ድጋፍ ለሌሎች አካባቢዎች በአርአያነት ይጠቀሳል ብለዋል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድም አገኘሁ የልማት ሥራዎቹን ሲመርቁ እንደተናገሩት አርሶ አደሮቹ  ከከተማው እድገትና መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመጣውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ  ያከናወኑትን ተግባር በዞኑ ገጠርና ከተሞች ጭምር እንዲስፋፋ ይደረጋል። ከአካባቢዉ ነዋሪዎች  መካከል ወይዘሮ ፀሐይ እሸቴ በሰጡት አስተያየት በካሣ የተከፈላቸው ገንዘብ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት ለመፍታት ለጋራ ጥቅም ለሚውሉ ተግባራት እንዲውል ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የዕድገት በጋራ ደን ልማት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት መለሰ ተሾመ በበኩሉ በከተማው የተከናወኑት የልማት ሥራዎች በመንገድ እጦት  ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ የነበረባቸውን ችግር እንደሚያቃልላቸውና ገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚያስችላቸው ገልጿል። በከተማው ዘንድሮ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚሆንባቸው ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ከከተማዉ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም