መውለድ በዓል ሲከበር መረዳዳትን ፣ ሰላምና መቻቻልን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ

146
ሀረር/ደብረብርሀን  ህዳር11/2011 ህዝቡ ሙስሊሙ የነቢዩ መሐመድ ልደት /መውሊድ/ በዓልን ሲያከብር  መረዳዳትን ፣ሰላም ፣ ፍቅርና  መቻቻልን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች አመለከቱ፡፡ 1ሺህ 493ኛው የነቢዩ ሙሐመድ  የመውልድ በዓል በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ እና በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ከተማ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል፡፡ በኮምቦልቻ ወረዳ ሰመርጌል ቀበሌ  በሚገኘው ሼህ ሐጂ መሐመድ ሳልህ መጅሊስ  በዓሉ ሲከበር የኦሮሚያ  ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት  ፕሬዝዳንት ሼህ አህመድ ዛኪር እንደተናገሩት እስልምና ሰላም፣ፍቅርና የአንድነት፣አብሮ የመኖርን ባህል የሚያጠናክር እምነት ነው፡፡ " በዓሉን ስናከብር ምዕመናኑ የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳትና በመንከባከብ ማክበር ይኖርብናል "ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ዜጎችን ከቄያቸው በማፈናቀል የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን  ተግባር የእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮት የማይቀበለው በመሆኑ ወጣቱ ሊከላከለው እንደሚገባም መክረዋል። የኃይማኖት አባቶች ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ረገድ የማስተማር ስራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ የእስልምና እምነት የሰላምና ተቻችሎ የመኖር ኃይማኖት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአዳማ አቡቡሬራ መስኪድ ኢማምና ኸጢብ ሼህ ሀጂ አሊ ወረባቡ ናቸው፡፡ ከተከታዮቻቸው ጋር የተቸገረ ወገናቸውን በመርዳት፣  ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ባህልን በሚያጠናክሩ ዝግጅቶች በዓሉን እንደሚያሳልፉት ተናግረዋል። ሼህ ሙሄዲን መሀመድ  በበኩላቸው " እስልምና የሰላም ኃይማኖት በመሆኑ ወጣቱ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይገባል፤ በተረጋጋ መንገድም መጓዝና ማስተዋል ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡ በሺዎች  የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በዓሉ ሲከበር የነብዩ መሀመድ ታሪክና አስምህሮት በኃይማኖት አባቶች የቀረበ ሲሆን  የምስጋና ዜማዎች በመስኪዱ ተማሪዎች ቀርቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓሉ በደብረብርሃን ከተማ ፍትህ መስጅድ ሲከበር የሰሜን ሸዋ ዞን እስልምና ጉዳይ ጽህፈት ቤት  ተወካይ ሼህ ነስሩ መሃመድ እንደገለጹት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የጥንት ባህሉንና ወጉን ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡ ረዳት የሌላቸውን አቅመ ደካማ ወጎኖችን  መርዳትና መደገፍ የበዓሉ አካል ሊሆን ይገባል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከሌሎች ኃይማኖት ተከታዮች ጋር በመቀናጀት   ፍቅራቸውን በመግለጽ ጥላቻን ፣  ክፋትንና  መተማማትን ማራቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ከበዓሉ ተካፋዮች መካከል አቶ ያሲን ጅብሪል በሰጡት አስተያየት ሙስሊሙ ማህበረሰብ በመካከሉ ያሉ ልዩነቶችና መቃቃርን አጥብቦ ወደ አንድ በመምጣት ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻውን ማበርከት እንደሚጠበቅበት  ተናግረዋል፡፡ በበዓሉ የነብዩ መሀመድ  ታሪክ፣ የእስልምና  አመጣጥና ሀዲሶች እየተነበቡ በድምቀት ሲከበር የኃይማኖት አባቶች፣ ኡላማዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶችም ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም