በትግራይ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተቀናጀ የጤና ኤክስቴንሽን መረሀ ግብር ተግባራዊ ሊሆን ነው

102
መቀሌ ህዳር 11/2011 በትግራይ ክልል ከ2 ሺህ 300 በላይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተቀናጀ  የጤና ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሓጎስ ጎድፋይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በትምህርት ቤቶቹ መርሀ ግብሩን ከታህሳስ 2011 አ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ። አስር የጤና ፓኬጆችን በመርሀ ግበሩ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። መርሀ ግብሩን በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገው ተማሪዎች ስለጤና ያላቸው አሰተሳሰብና ግንዛቤን በማሳደግ ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ ለማፍራት መሆኑን ገልጸዋል። "በተጨማሪም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትልቅ ድርሻ እንዳለው በመታመኑ ነው " ብለዋል ። "በክልሉ ከ1ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ተማሪዎችና ከ55 ሺህ በላይ መምህራን አሉ " ያሉት ኃላፊው በተቋማቱ ውስጥ መስራት በሽታዎች ከመከሰታቸው በፊት ለመከላከል አማራጭ ዘዴ መሆኑን አብራርተዋል ። በትምህርት ተቋማት ያሉት የተማሪዎችና የመምህራን ቁጥር ከአጠቃላይ የክልሉ ህዝብ 30 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል ። "መርሀ ግብሩ በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መደረጉ አጠቃላይ 90 በመቶ የሚሆነው የክልሉ የህብረተሰብ ክፍል በጤና አጠባበቅ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስችላል " "ብለዋል ። በየትምህርት ቤቶች ያሉት የጤና ክበቦች፣ መምህራን፣ የወረዳ ትምህርትና የጤና ፅህፈት ቤቶች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተቀናጀ መልኩ በመርሀ ግብሩ ትግበራ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል ። እንደ ኃላፊው ገለጻ ለመርሀ ግብሩ ማስፈፀሚያ የሚውለው በጀት በጤናው ዘርፍ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በድጋፍና ከህብረተሰቡ በሚሰበሰብ  የሚሸፈን ነው ። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው "በትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የግላቸው፣ የመማሪያ ክፍሎችን የመጸዳጃ ቤታቸውንና የመማሪያ አካባቢዎችን በማጽዳትና በማስዋብ ጭምር ይሳተፋሉ" ብለዋል ። በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት አንዳንድ ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን ትምህርት የመቀበል የአቅም ውስንነት ለመፍታት መርሀ ግበሩ አስተዋጻ እንደሚኖረው ምክትል የቢሮ ሀላፊው ተናግረዋል ። እንደ ምክትል የቢሮው ኃላፊ ገለጻ የየትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ተማሪዎችና ወላጆች የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር በመርሀ ግብሩ ትግበራ ይሳተፋሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም