በሰሜን ሸዋ ዞን 96 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ስራ በመካሄድ ላይ ነው

1197

ደብረብርሀን ህዳር 11/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወራት 96 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም የድህረ ምርት አያያዝ ባለሙያ አቶ ሁሉምይፈር ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ዘንድሮ በመስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 11 ሺህ ሄክታሩ በቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ሰብል የሚሸፈን ነው፡፡

ቀሪው ደግሞ በጥራጥሬ፣ አዝርእት፣ ቅመማ ቅመምና ሥራሥር ሰብሎች አንደሚለማ ገልፀዋል፡፡

የመስኖ ልማቱ የሚካሄደው አርሶ አደሩ በክረምት ወቅት ባጠራቀመው የዝናብ ውሃ፣ ወራጅ ወንዞችን በመጥለፍና ምንጮችን በማጎልበት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም የመኸር አዝመራን በመሰብሰብ ለመስኖ ልማት የሚውል ማሳ የማዘጋጀትና የማልማት ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን በተካሄደው ስራም ከ23 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ መልማቱን የገለፁት አቶ ሁሉምይፈር በልማቱ  46 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ በሚካሄደው የመስኖ ልማት  15 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም አብራርተዋል፡፡

በቀወት ወረዳ የየለን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ወንድምአፈራሁ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት የክረምት ዝናብን ሳይጠብቁ ወንዝ በመጥለፍ የመስኖ ልማት በማካሄድ ኑሯቸውን ማሻሻላቸውን ገልፀዋል፡፡

ከመስኖ ልማቱም በየአመቱ ከ300 ኩንታል በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ስራ ስር በማምረት አመታዊ የምግብ ፍጆታቸውን ከመሸፈን ባለፈ ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ በሽዋሮቢት ከተማ የመኖሪያ ቤት መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

በያዝነው ዓመትም በአንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ድንች በመስኖ እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ካለሙት ማሳ ያገኙትን 200 ኩንታል የሽንኩርት ምርት ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሞጃና ወደራ ወረዳ  የአባበርሶማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታደሰ አመጸ በበኩላቸው በበጋ ወቅት የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት ኑሯቸውን ማሻሻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲለ የክረምት ዝናብ በመጠቀም ከእጅ ወደ አፍ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው በአካባቢያቸው የተሰራውን ግድብ በመጠቀም በመስኖ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ዘንድሮም በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ምስር፣ ካሮትና ጥቅል ጎምን በማልማት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሶስት ዙር ከሚያካሂዱት የመስኖ ልማት ከ100 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ያቀዱ ሲሆን እስካሁንም 15 ኩንታል ሽንኩርት በማምረት ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው ዓመት 89 ሺህ 332 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 14 ሚሊዮን 280 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን ከመምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡