በሐረሪ ክልል የሕግ የበላይነት አለመከበር ነዋሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል

1205

አዲስ አበባ  ህዳር 11/2011  በሐረሪ ክልል የሚታየው የህግ የበላይነት አለመከበር ስጋት እንደፈጠረባቸው የከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የክልሉ ፀጥታና ፍትህ ጉዳዮች ቢሮ በበኩሉ የህግ የበላይነት አለመከበር ጉዳይ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚያስፈልገው እንደሆነ ገልጿል።

የፍቅርና የሰላም ከተማነቷ የምትታወቀው ጥንታዊቷ ሐረር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላሟ እየታወከ ነዋሪዎቿ በፀጥታ ችግር ስጋት ውስጥ ገብተዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ በአካባቢው ያለው የፀጥታ መደፍረስና የህግ የበላይነት አለመከበርን ለማስተካከል መንግስት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት።

አቶ ነስሩ  ጃሚ “እኛ የምንለው የህግ የበላይነት ይከበር ነው፣ የህግ የበላይነት እየተከበረ አይደለም፣ ሐረረ ከተማ  በጣም አስቸጋሪ ነው። ”  ብለዋል ፡፡

”ስርዓት አልበኝነት  በመንገሱ  የሰው ቤት ተሰብሮ  በመግባት  ንብረት ይወስዳል። ”  ያሉት ደግሞ  አቶ ረምዚ አብዱልከሪም  ናቸው፡፡

 በሐረር ከተማ ከሚስተዋሉ ስርዓት አልበኝነት ተግባራት ለአብነት ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በሚስተዋልባቸው የከተማዋ ስፍራዎች የሚዘዋወሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸው መሆናቸውን የኢዜአ ሪፖርተር መታዘብ ችሏል።

በስፍራው በትራፊክ ቁጥጥር ሥራ ላይ የተሰማሩት ኮንስታብል መሐመድ አብዱሬ በሐረር ከተማ የመንግስትና የግል ተሽከርካሪዎችን መቆጣጠር ለትራፊክ ፖሊሶች ከባድ ፈተና እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመንግስትና በግል ተሽከርካሪዎች ላይ የሚደረግ ቁጥጥር ጫና ያለበት መሆኑን ጠቁመው ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ላይ ቁጥጥር እንዳይካሄድም ባለንብረቶች በቡድን ተደራጅተው በተቆጣጣሪ ትራፊክ ፖሊሶች ላይ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በትራፊክ ተቆጣጣሪ ፖሊሶች ላይ የሚደርሰውን በደል ኃላፊነት የሚወስድ አካል ባለመኖሩ ተሽከርካሪዎችን በህግ አግባብ መቆጣጣር አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ኮንስታብል መሐመድ አመልክተዋል።

የክልሉ ጸጥታና ፍትህ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አበበ መብራቱ እንዳሉት፤ በሐረሪ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ማንኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች የጸጥታና ፍትህ እጦት ችግር ያለበት አካባቢ ነው።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሐረሪ ክልል ተግባራዊ ሳይሆን በመቆየቱ በህዝቡ ዘንድ ያለው ቅሬታና እሮሮ ሳይፈታ በመቅረቱ በክልሉ ሁከትና ብጥብጥን እንደ መፍትሄ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

“የህግ የበላይነት ጉዳይ ምንም የሚያደራድር አይደለም” ያሉት አቶ አበበ የሐረሪ ክልል ሁኔታ ለየት ያለ ባህሪ እንዳለውም ገልጸዋል።

በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈንና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ጠንካራ የፀጥታ አካላትን በማብዛት ብቻ የሚመለስ ሳይሆን ሳይንሳዊ የሆነ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሻ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሐረር ከተማ የጸጥታ ሁኔታ ተስፋ የሚታይበት እንደሆነ የገለጹት አቶ አበበ ችግሩ ሰፊ በመሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የህዝቡን ጥያቄ ሊመልሱ የሚችሉ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን መዘርጋት የሚጠይቅ እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል።