ያልተጠቀምንበት ሀብት በሀረር !

123
አዳም ካሳሁን (ኢዜአ ) በሐረር ከተማ በተለምዶ ደከር በሚባል አካባቢ የሚገኘው የአብርሃ ባህታ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል በትውልድ ኤርትራዊ በሆኑት አቶ አብርሃ ባህታ በ1958 ዓ.ም እንደተቋቋመ ይነገራል። በወቅቱ 13 አረጋዊያንን በመንከባከብ ነበር ስራ የጀመረው። በ1962 ዓ.ም ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ፈቃድ ረዳትና ደጋፊ ያጡ ዜጎችን የመጦር ሃላፊነት ተሰጠው። ከዚህ ተልእኮው ጎን ለጎን ለወጣቶች የሞያ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ ዓለም የማሰማራት ሃላፊነትም ተጥሎበት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። ያም ሆኖ ግን ዓመታዊ በጀቱ ከ70 ሺህ ብር የዘለለ አልነበረም። ሐረር ከተማ በአሁኑ ወቅት በየሐይማኖት ተቋማቱ፣ በየመንገዱና በየጥጋጥጉ በርካታ አረጋዊያን መኖሪያና ማደርያ አጥተው ሲንገላቱ ማየት የተለመደ ነው። ገሚሱ ደግሞ አቅሙን ጨርሶና የሚነሳው አጥቶ እስከ ወዲያኛው …. ። በክልሉ እንኳን ለራሱ ለሌሎች የሚተርፍ የአብርሃ ባህታ የአረጋውያውን መርጃ ማዕከል እያለ ረዳትና ደጋፊ ያጡ አንዳንድ አረጋውያን ከቀዬአቸው ርቀው ወደ ሌሎች የአረጋውያን ማረፊያ ማዕከላት እንዲጓዙ የሚገደዱበት አጋጣሚ መኖሩን የዓይን እማኞች ይመሰክራሉ። በቅርቡ እንኳን 10 የሚደርሱ አረጋዊያን ከሀረር ወደ መቆዶኒያ መሄዳቸውን ይነገራል። አረጋውያኑ ድጋፍና ክብካቤ ፍለጋ ከአካባቢያቸው ርቀው ለመሄድ የተገደዱት በአቅራቢያቸው ያለውን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚያውለውና ትኩረት የሚሰጠው አካል በመታጣቱ ነው። በሀረርና አካባቢው በአደንዛዥ ሱስ ምክንያት ከአዕምሮ ህመም ጋር እየታገሉ የሚኖሩ ወጣቶች በርካታ ናቸው። ይህን ታሳቢ ያደረገ ለማስተማሪያና ለማገገሚያ አገልግሎት የሚሆን ዘመናዊ ህንፃም  በማእከሉ ጊቢ ተገንብቶ ነበር ። ትኩረት በማጣት ግን የታለመለትን አገልግሎት መስጠት አልቻለም። እንዲያውም ለሌላ ዓላማ ሊውል ነው የሚል ወሬም መናፈስ ጀምራል። አራት በበጎ አድራጎት ስራ የተሰማሩ አገር አቀፍ ድርጅቶች ማእከሉን ለማስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርቡም ከሚመለከተው አካል ምላሽ ሊሰጣቸው አልቻለም። ከ8 ሄክታር መሬት በሚበልጥ መሬት  ተንጣልሎ የሚገኘው ጊቢ 6 አረጋዊያንና 32 ሰራተኞች ብቻ ይዞ ያለተገቢ አገልግሎት ተቀምጧል። የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር በ75 ሚሊየን ብር ወጪ በጊቢው ያስገነባው የሰው ሰራሽ እግር ተከላ ህንፃ ከነሙሉ መሳሪያዎቹ ላለፉት 11 ዓመታት ያለስራ በአረም ተውጦ የሰው ያለህ ይላል። በከተማው ለአምስት አስርት ዓመታት ለአረጋዊያን አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውና ትኩረት የተነፈገው የአብርሃ ባህታ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከልን የሚመለከተው አካል ሊታደገው ይገባል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎችና የማዕከሉ ሰራተኞች ይጠይቃሉ። ማዕከሉ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለማድረግ እየሰራሁ ነው ሲል የክልሉ ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ይገልጻል። በማዕከሉ ለ25 ዓመት በወጥ ቤት ስራ ያገለገሉት ወይዘሮ ወይንሸት ግዛው “ማዕከሉ የአረጋዊያን፣ የአካል ጉዳተኛና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ነበር ። በጊዜውም አልባሳት፣ ምግብና ሳሙና በተሟል መልኩ ይቀርብ ነበር ። ጊቢውንና የማእከሉ ተጠቃሚዎች የሚንከባከቡ በቂ የፅዳት ሰራተኞችም ነበሩት። አሁን አሁን ሁሉም የለም።  ገሚሶቹ የማክሉ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ሲዳረጉ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ ሌላ ስፍራ ሄዱ ይላሉ።  በማዕከሉ ከነበሩት 42 የወተት ላሞች መካከል 40ዎቹ ተንከባካቢ በማጣታቸው ሞተዋል።  በአሁኑ ወቅት ሁለት ብቻ ነው የቀሩት ይላሉ። የክልሉ መንግስት በሚደጉመው የምግብና ለሰራተኞች በሚከፍለው ወርሃዊ ደመወዝ 6 አረጋዊያን ብቻ በማዕከሉ ይገኛሉ። አልባሳትና የተመጣጠነ ምግብ ከግለሰብ ነው የሚገኘው። ስለዚህ መንግስት ትኩረት ይስጥበት የሚለውን የብዙሃኑ ጥያቄ ነው። በደከመ አንደበታቸው ፈራ ተባ እያሉ ያነጋሩን የ77 ዓመት እድሜ  ባለፀጋ አቶ ጉተማ አመንሲሳ በደከመ አንደበታቸው “በ1992 ዓ.ም ወደ ማዕከሉ መቀላቀላቸውንና በሂደትም አረጋዊያኑ በሞትና በማያውቁት ነገር እየተመናኑ መምጣታቸውን” ተናገረዋል። “እንበላለን፤ እንጠጣለን፤ ግን ለምን ሰው አይገባም አሊያም አይመጣምስ? የሰው ያለህ ሰው ብቻ አምጡልን ይህንንም ለሚመለከተው አካል መልዕክት አስተላልፉልኝ” ሲሉ በተማጽኖ ጠይቀዋል። በማዕከሉ ከ14 ዓመት በፊት ስቀጠር አረጋዊያኑ በሳምንት ሁለት ቀን ስጋ ይመገባሉ። በበዓል ቀን ደግሞ ከብት ይታረድላቸዋል ያሉት የማዕከሉ ሰራተኛ ወይዘሮ ንጋቷ ፍራ አሁን ግን ሁሌም አንድ ዓይነት ምግብ መመገብ ግድ ሆኖባቸዋል። ህዝቡ ግን በየበዓዕቱ ያለውን ይዞ በመምጣት እና በማልበስ የጽድቅ ስራ እየሰራ ይገኛል ባይናቸው ። በማዕከሉ ስማቸው መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ የአለም ቀይ መስቀል ማህበር ግንባታውና ቁሳቁሶቹን ጨምሮ 75 ሚሊየን ብር ወጪ የወጣበት የሰው ሰራሽ እግር ተከላ መሳሪዎችና ህንጻዎች ከአስርት ዓመታት በላይ ያለስራ መቀመጡን ገልፀው በሁኔታው ማዘናቸውን ተናግሯል ። ይህ እስከመቼ ሊዘልቅ ይችላል? በማዕከሉ ያሉት አረጋዊያንም የሰው ያለህ እያሉ ነው ። ሰራተኛውም አለስራ ዝም ብሎ በመቀመጡ ስጋት ላይ ይገኛል ።  መፍትሄ !!!!። ”ተወልጄ የደኩት ሐረር ነው፤ አብረሃ በሀታንም ከልጀነቴ ጀምሮ አውቀዋለው አረጋዊያን ሲገቡበት፣ ሲነከበከቡበት፣ ሲያርፉበትና ሲጦሩበት ነበር የምናውቀው ” ያሉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሙልጌታ ጥላሁን ናቸው። አሁን አሁን ግን ማዕከሉ በአረም ተወሮ ህንጻው ተሰነጣጥቆና ባዶ ሆኖ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲሉ በምሬት ያስረዳሉ። በከተማው አረጋውያን በየቤተክርስትያኑ፣ በየመስጊዱ እና በየአጥር ጥጋጥጉ ወድቀው ነዋሪዎች የአቅማቸውን በመደገፍ እየረዱዋቸው ይገኛል። ማዕከሉ ግን ባዶውን ተቀምጧል። እድሜ ነውና ነገ ሁሉም ወደ እርጅና ይሄዳል። በተለይ አመራሩ እናትና አባት አለው።  ህሊና ካለን ማዕከሉን እንታደግ አሊያም ለሚሰራ አካል ይሰጥ የሚል የሁሉም ጥያቄ ነው። የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የክልሉ የማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት  ግን የተወሰነ ምላሽ ሰጥቷል። የዕህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አብዱለዚዝ መሀመድ ሲመልሱ በከተማው የሚገኘው የአብርሃ ባህታ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል በክልሉ ለበርካታ ዓመታት አረጋዊያንን የሚረዳ ማዕከል ነበረ። በአሁኑ ወቅት በውስጡ ጥቂት አረጋዊያን ቢኖሩም የአገልግሎት አሰጣጥ ስራው እየተከናወነ ነው ለማለት ያስቸግራል ይላሉ። የክልሉ መንግስት ማዕከሉን የአረጋዊያን፣ የአዕምሮ ህሙማንና ሌሎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለማድረግ የአዲስ ዲዛይን ስራ እየተከናወነ ይገኛል ቢሉም መሬት ላይ የሚታይ ነገር ግን የለም። የኢትዮድያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በጊቢው ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ለአዕምሮ ህሙማንና ለአረጋዊያን መርጃ ማዕከል በተንጣለለው መሬት ላይ የተገነቡት ህንጻዎች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛ የእግር ተከላ የተገነቡት ህንጻዎችና የተተከሉት ማሽኖት ባለቤት አጥተው ሳር በቅሎባቸዋል። በውስጡ የሚገኙ ስድስት አረጋዊያን አብሯቸው የሚኖሩ ተመሳሳያቸውን በአይናቸው ለማየት በተስፋ  ይጠባበቃሉ።  ሰራተኞችም ተስፋ የሚዘራላቸው አካልን ይሻሉ። ነገር ግን በክልሉ በርካታ አረጋዊያን ማረፊያ አጥተው ባሉበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ማዕከል አለ ስራ መቀመጡ ቁጭት የሚያሳድር በመሆኑ እኔ አለሁልህ የሚል ሰው ያስፈልገዋል።  ሊሰራበትም ይገባል። የቅርብ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓይነት የመቆዶኒያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ጉብኝትን ጭምር ይሻል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም