አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን በሲያትል ከኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ

1931

አዲስ አበባ ህዳር 11/2011 አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን በአሜሪካ ሲያትል አካባቢ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ከማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ።

ውይይታቸው ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት የዳያስፖራው ተሳትፎ በሚኖረው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮረ ነው።

አምባሳደሩ ለኢትዮጵያ መዋቅራዊ ለውጥ እድገት የዳያስፖራው ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በሲያትል የሚገኙ የማህበረሰብ ተወካዮች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ዋሽንግተን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ሎስ አንጀለስ ካለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ጋር በየጊዜው በመገናኘትና በመመካከር ትስስሩን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አምባሳደሩ አሳስበዋል።

የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ለዳያስፖራው ጉልህ ተሳትፎ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መደረሱንም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።