አንድ ሺህ 493ኛው የነብዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል ተከበረ

100
አዲስ አበባ ህዳር 11/2011 1 ሺህ 493ኛው የነብዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጅድ በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ እየተከበረ ሲሆን በአንዋር መስጅድም በሺዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች በታደሙበት ነው የተከበረው። ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማሰብ እንዲሆንም የሃይማኖት አባቶች መክረዋል። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳት ሀጅ ኑርሁሴን መሐመድ በዓሉ ነብዩ መሐመድ የሚወደሱበትና የሚታሰቡበት ነው ብለዋል። ነብዩ መሐመድ ለሰው ልጆች ሁሉ በጎ ማድረግን ለተከታዮቻቸው ማስተማራቸውንና የመልካም ተግባር ምሳሌ መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ሙስሊሙ ማህበረሰብ በበዓሉ ቀን የተቸገሩ ወገኖችን በማብላት፣ በማጠጣት፣ በማልበስና በመጎብኘት እንዲያከብሩት አሳስበዋል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ነብዩ ያስተማሩትን ሰላም፣ መረዳዳት፣ ፍቅርና መከባበርን በመተግበር እርስ በእርሳቸው በመዋደድና በአንድነት መኖር እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ሼህ ዑመር ይማም በበኩላቸው በዓሉ በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበር ቢሆንም ህዝበ ሙስሊሙ ነብዩ መሐመድን ሁሌም እንደሚያስባቸውና ስራቸውን እንደሚያስታውስ ገልጸዋል። ነብዩ መሐመድ በሙስሊምና ሙስሊም ባልሆኑት፣ በዘመድና በጎረቤት መካከል ብለው ልዩነት እንዳላስቀመጡና መልካምነታቸውም ለሙስሊሞች ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ላልሆኑትም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል። ነብዩ መሀመድ የተቸገሩና ረዳት የሌላቸውን መደገፍ የእስልምና እምነት ተከታዩች የዘወትር ተግባር እንዲሆን ማዘዛቸውን አስታውሰዋል። በታላቁ አንዋር መስጅድ የበዓሉ አከባበር ስነ ስርዓት የእምነቱ አባቶች ለምዕመኑ ትምህርት ሰጥተዋል። በነብዩ መሐመድ የመውሊድ በዓል ምሽት በመንዙማ የሚካሄደው ለፈጣሪ ምስጋና የማቅረብ ሥነ-ስርዓት ደማቅ፣ ተወዳጅና የተለየ ድባብ እንዳለውም አባቶቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም