በምሥራቅ ወለጋ በ14 አምቡላንሶች ለወረዳዎች ተከፋፈሉ

1040

ነቀምት ህዳር 11/2011 በምሥራቅ ወለጋ ዞን በሕብረተሰቡ ተሣትፎና በመንግስት በጀት በ15 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የተገዙ 14 አምቡላንሶች ለወረዳዎች መከፋፈላቸውን ዞኑ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሦናን ደሣለኝ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ለአምቡላንሶቹ ግዢ ከዋለው ገንዘብ ውስጥ 7 ሚሊዮን ብሩ በህብረተሰቡ ተሳትፎና ቀሪው ከክልሉ ጤና ቢሮ የተሸፈነ ነው።

አንቡላንሶቹ በተለይም የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ የቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጅማ አርጆ ወረዳ የጤና ጣቢያ ኃላፊ ወይዘሮ የሺ ምትኩ በጤና ጣቢያው ሁለት አምቡላንሶችን በድጋፍ ማግኘቱን ተናግረዋል ።

በጤና ጣቢያው በስራ ላይ ካሉት ጋር የአምቡላንሶች ቁጥር ወደ አራት ማደጉን የገለፁት ወይዘሮ የሺ የአምቡላንሶቹ ቁጥር ማደግ በተለይም የደም መፍሰስ የሚያጋጥማቸውን የድንገተኛ ህሙማንና ወላዶች ህይወት ለመታደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል ።

የስሬ ጤና ጣቢያ አዋላጅ ነርስ ሲስተር አመለወርቅ ታረቀኝ በበኩላቸው “ጤና ጣቢያው በድጋፍ ያገኛቸው አምቡላንሶች እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ እየተሰራ ያለውን ስራ ያጠናክረዋል” ብለዋል።

በሲቡ ስሬ ወረዳ የቡርቃ ጣሎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሽታዬ ነገራ በቅርቡ ድንገተኛ ምጥ በገጠማቸው ወቅት በተደረገላቸው የአምቡላንስ ድጋፍ በፍጥነት ወደ ጤና ጣቢያ በመድረሳቸው ልጃቸውን ያለጤና ችግር መገላገላቸውን ተናግረዋል።