በዞኑ በመስኖ ከሚለማው መሬት ከ826 ሺህ ኩንታል በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ይጠበቃል

1136

ሑመራ ህዳር 11/2011 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በጋ ወቅት በመስኖ ከሚለማው መሬት ከ826 ሺህ ኩንታል በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ፡፡

በአስተዳደሩ የመስኖ ልማት አስተባባሪ አቶ ብርሃነ ፍስሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት ምርቱን የተከዜ፣የካዛና የባህረ ሰላም ወንዞችን በመጠቀም 5 ሺህ 753 ሄክታር መሬት ለማግኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በልማቱ ከሰባት ሺህ በላይ  አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉና ከነዚህም ከሦስት ሺህ በላይ የሚሆኑት ወጣትና ሴት አርሶ አደሮች መሆናቸውን  አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ለልማቱ የመኸር ሰብላቸውን በማንሳት መሬታቸውን በማዘጋጀትና የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎችን እያሰባሰቡ ናቸው ብለዋል፡፡

ለልማቱ የሚውል 6ሺህ 748 ኩንታል ማዳበረያና 484 ኩንታል ምርጥ ዘር መዘጋጀቱንም አቶ ብርሃነ ተናግረዋል፡፡

ሰሊጥ ብቻ በማምረት ተወስኖ የነበረው የአርሶ አደሮች ፍላጎት አሁን በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ዕድገት እያሳየ መምጣቱን  አስተባባሪው አመልክተዋል፡፡

የአሥረኛ ክፍል ትምህርቱን በማጠናቀቅ በመስኖ ልማት ሥራ እንደተሰማራ የተናገረው ደግሞ የሰቲት ሑመራ ነዋሪ ወጣት ሄኖክ ደምሴ ነው፡፡

የተከዜ ወንዝን በመጠቀም በግማሽ  ሄክታር መሬት ላይ ቀይ ሽንኩርት፣ቲማቲምና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

ከዚህም 75ሺህ ብር ገቢ አገኛለሁ ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጿል፡፡

ከልማቱ 45ሺህ ብር ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸው የተናገሩት ደግሞ የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሰሎሞን መብራህቱ ናቸው፡፡

በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ባለፈው ዓመት 4 ሺ125 ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቶ 598 ሺህ 446 ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት መገኘቱን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡