በኦሮሚያ ክልል 120 ቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርቱን በቀጥታ ለዓለም ገበያ ሊልኩ ነው

89
አዳማ ህዳር 11/2011 በኦሮሚያ ክልል ከ120 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸው ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለፁ፡፡ የባለስልጣኑ ኃለፊ አቶ ዳባ ጅንፌሳ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በቡና ልማት የተሰማሩ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ዓመታዊ ምርታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት በቀጥታ ቡናን ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በዚህም ባለፈው የበጀት ዓመት 123 አርሶ አደሮች ፍቃድ እንዲያገኙና ቡና ወደ ዓለም ገበያ መላክ እንዲጀምሩ መደረጉን  ጠቅሰዋል። አርሶ አደሮቹ  የሚያመርቱት ቡና አንድ ኮንተይነር መሙላቱ ከተረጋገጠ ቀጥታ ምርቱን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበት አሰራር መፈጠሩን ተናግረዋል ። አሁን በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ በቡና ግብይት ላይ የሚታየውን  ህገ ወጥ ንግድ ለማስቀረት ያለመ ከመሆኑም በላይ አምራች አርሶ አደሩና ሀገሪቱ ከሀብቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ። ''ክልሉ ሀገሪቱ ከምታመርተው ጠቅላላ የቡና ምርት 70 በመቶውን ድርሻ  እንደሚይዝ የተናገሩት አቶ ዳባ ምርቱ ወደ ማእከላዊ ገበያ ሳይቀርብ በህገ ወጥ መንገድ እንደሚወጣ በጥናት አረጋገጠናል'' ብለዋል። በዘንድሮ የበጀት ዓመት ለማእከላዊ ገበያ 250 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለማቅረብ ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጨምሮ ገልጠዋል። በአሁኑ ወቅት ከ70 ሺህ ቶን በላይ የተፈለፈለ ቀይ እሸት ቡና ለማእካለዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑንና በዚህም የአርሶ አደሩ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን ተናግረዋል። በማምረት አቅማቸው ተመዝነው ቡናን ቀጥታ ወደ ውጭ እንዲልኩ ፍቃድ ካገኙት አርሶ አደሮች መካከል በአርሲ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ የወረጉ ቀዌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር  አርሶ አደር ነስሮ አሊይ አንዱ ናቸው። በየዓመቱ ከ10 እስከ 15 ሄክታር መሬት ቡና እንደሚያለሙ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የቡና መፈልፈያ ማሽን በመትከል  ራሳቸውን ያመረቱትና በግዥ የሚሰበስቡትን ጨምሮ በየሁለት ሳምንቱ በአማካይ 400 ኩንታል ቡና እያዘጋጁ ለማእከላዊ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል። ''በዘንድሮ ዓመት  አርሶ አደሮች በቀጥታ የቡናን ምርት ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ መንግስት ሁኔታ በማመቻቸቱ ፍቃድ አግኝቼ ከ5 ሺህ ኩንታል በላይ ቡና ወደ ውጭ ለመላክ እየሰራሁ ነው'' ብለዋል፡፡ ሌላኛው አስተያያት ሰጪ በወረዳው የጫንጮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኢሳቅ ሀሰኖ በበኩላቸው  የአርሲ ጎለልቻ ቡናን ድሬዳዋ ወስደው ለማእከላዊ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ''በአሁኑ ወቅት ደግሞ በጥራት አዘጋጅቼ ለማቀርበው ቡና ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልኛል'' ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም