የመገናኛ ብዙሃን የህፃናትን ጉዳዮች በተመለከተ የሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች ደካማ ናቸው – አንድ ጥናት

4112

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2010 የመገናኛ በዙሃን በህፃናት ላይ የሚደርሱ ችግሮችና መፍትሄዎችን በተመለከተ የሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች ደካማ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በኢትዮጵያ የህጻናትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አስመልክቶ የመገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቧቸውን ዝግጅቶችና ሌሎች መረጃዎች ዳሰሳ ጥናት  በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አድርጓል፡፡

ከሱማሌ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በጥናቱ ተሳተፈዋል፡፡

በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሰጡት ምላሽ ህጻናትን በተመለከተ በብሮድካስት መገናኛ ብዙሃኖች የሚቀርቡ ዝግጅቶች “በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉ ህጻናትን አያካትቱም” ብለዋል፡፡

የህትመት መገናኛ ብዙሃን የህጻናትን ጉዳይ በተመለከተ ራሱን የቻለ ቋሚ አምድ እንዳላቸው አመልክተው፤ የይዘትና ጥራት ችግር እንደሚስተዋልባቸው ነው 54 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች የገለጹት፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን ከህጻናት ጋር በተያያዘ በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡት ርዕሰ ጉዳዮች የህጻናቱን የእውቀት አድማስ የሚያሰፉና የሚያዝናኑ መሆናቸውን እንደአንድ ነጥብ ተወስዷል፡፡

መገናኛ ብዙሃን የልጆችንና ህጻናትን ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በህጻናት ላይ የሚደርሱ አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ጉዳቶች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተጠቆመው፡፡

ለዚህ ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር መገናኛ ብዙሃን የሕጻናት ፕሮግራሞች  አዘገጃጀት ላይ ስርዓተ ትምህርት በመቅረፅ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስልጠና እንዲሰጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት  እንዳለበትም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

በህፃናት የመገናኛ ፕሮግራሞች ላይ ማስታወቂያዎችን የማስነገርም ሆነ ፕሮግራሞቹን ስፖንሰር የማድረግ ፍላጎት እጅግ አናሳ መሆኑን አመልክቶ፤ መንግስት በቂ በጀት በመመደብ የፕሮግራሞቹን ጥራትና ተደራሽነት ለማጠናከር ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል፡፡