የአስፓልት መንገድ ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን በባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

73
ጎባ ህዳር 10/2011 ባሌን ከአርሲ ዞን የሚያገናኘው የአስፋልት መንገድ እንዲሰራላቸው ለዘመናት ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን በባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የአሊ-አጋርፋ አርሲ-ሮቤ 53 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የመንገድ ልማት ዘርፍ ዕቅድ አካል መሆኑን አስታውቋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል በ90 ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ሐጂ ኢብራሂም በከሩ እንደተናገሩት መንገዱ ወደ አስፋልት ደረጃ እንዲያድግ ለዘመናት ሲጠይቁ ነበር፡፡ መንገዱ ባለመስተካከሉ የተነሳ በአካባቢያቸው የሚያመርቱትን የአትክልትና ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶቻቸውን ፈጥነው ለገበያ በማቅረብ በሚፈልጉት ዋጋ ለመሸጥ አለመቻላቸው የዘመናት ቁጭት ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ "የትውልዶች ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ በህይወት ቆይቼ በማየቴ ዳግም እንደተወለድኩ ነው የምቆጥረው" ብለዋል ሐጂ ኢብራሂም፡፡ ባሌን ከአርሲ ዞን ጋር በአጭር ርቀት የሚያገነኘው መንገድ ወደ አስፋልት እንዲያድግ በመንግስት መወሰኑ በደላላ ስንነጠቅ ከነበረው ምርታችን በተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን ያደርገናል" ያሉት ደግሞ የወረዳው የሀገር ሽማግሌ ሼህ አብዱሰላም አደም ናቸው፡፡ ከአጎራባች የአርሲ ዞን ጋር ያላቸውን ማህበራዊ ትስስርንም ያጠናክረዋል የሚል እምነት እንዳለቸው ነው የገለጹት። መንገዱ ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከመንግስትና ከሥራ ተቋራጩ ጋር በመተባበር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ "በዞኑ ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ግንባታቸው ተጀምሮ የተቋረጡ የሮቤ-ጋሰራ እና የጋሰራ- ጊኒር መንገዶች እጣ ፋንታ እንዳይገጥም መንግስትና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቀለን" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዜይኒ አብዱረህማን ናቸው፡፡ ከራሳቸው የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብሬ ኡርጌሶ በበኩላቸው "መንገዱን ወደ አስፋልት ኮንክሪት ለማሳደግ መወሰኑ መንግስት የህዝቡን ሁለንተናዊ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ የገባውን ቃል በተግባር መተርጎሙን ያሳያል" ብለዋል፡፡ የአጋርፋ ብሎም የባሌ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ የነበረው መንገድ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠናቆ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ "በቀጣይም ህዝቡ በአገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጦች ከግብ እንዲደርሱ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ፊቱን ወደ ልማት መዞር አለበት" ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱረህማን በበኩላቸው “የአሊ አጋርፋ አርሲ ሮቤ 53 ኪሎ ሜትር አንደኛ ምዕራፍ የመንገድ ፕሮጀክት የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የመንገድ ልማት ዘርፍ ዕቅድ አካል ነው" ብለዋል፡፡ መንገዱን ከጠጠር ወደ አስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ለማሳደግ መወሰኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደጉም  በላይ በዙሪያ ጥምጥም ይገናኙ የነበረው የአርሲና የባሌ ዞኖችን በአጭር ርቀት እንደሚያገናኝ አመልክተዋል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቱን ግንባታ የሚያካሄደው “ሲሲሲሲ” የተባለ የቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ሥራ ተቋራጭ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዳይሬክተሩ ለመንገዱ 2 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን አስታውቀዋል፡፡ ለመንገዱ ግንበታ የተመደበው በጀት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን የግንባታ ሥራውንም በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከሥራ ተቋራጩ ጋር የኮንትራት ውል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ የቻይናው “ሲሲሲሲ” ሥራ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ታዎ ኮንት በበኩላቸው ካምፓኒያቸው ባከበተው የረዥም ጊዜ የሥራ ልምድ በመጠቀም የመንገዱን ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ በጥራት ሰርቶ ለማስረከብ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በባሌ ዞን የአሁኑን መንገድ ጨምሮ የሮቤ-ጋሰራ፣ የጋሰራ -ጊኒር፣ የሮቤ -ጎሮና ሮቤ -ደሎ መና የጠጠር መንገዶችን ደረጃ ወደ አስፈልት እንዲያድግ የዞኑ ህዝብ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሳባቸውና የመልካም አስተዳደር ጥያቄም እንደነበሩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም