ቆም ብለን …

56
ደሞዝ አያሌው ኢዜአ በርካታ የአለም ሀገራት የማህበራዊ ሚዲያ ቴክኖሎጂን በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና በፖለታካዊ ዘርፎች ለተጎናጸፉት ውጤት ሁነኛ መሳሪያ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በተቃራኒው ከነበሩበት የእድገት ሂደት እና ከሰላማዊ ህይወት አሽቆልቁለው ማንም አካል አትራፊ ወዳልሆነበት በእርስ በርስ ጦርነት ሀገራቸውን አፍርሰው ለዜጎቻቸው ሞት፣ በረሀብ አለንጋ መቀጣት፣ ለወረርሽኝና  ስደት መዳረግ እጣፈንታቸው እንዲሆን የጥላቻና የሀሰት መረጃዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ በተለያዩ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ይፋ እየተደረገ ነው፡፡ በሚወርድባቸው የከባድ ጦር መሳሪያ ወደ ፍርስራሽነት በመቀየር ላይ ያሉትና እስካሁን መቋጫ መፍትሄ ያላገኘው የመካከለኛው መስርቅ የቅድመ ስልጣኔ ምድር የነበረችው ሀገረ ሶሪያን እና ለኢትዮጵያ የቅርብ ጎረቤት በሚባል አቅራቢያ የምትገኘው  የመን  በምሰሌነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ለዜጎቿ ህይወት የሚበጁ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ዘመኑ ከፈጠረው የማህበራዊ ሚዲያ ቴክኖሎጂ መጠቀም የምትችልበት ምቹ ሁኔታዎች እየሰፋ ቢመጡም በተቃራኒው በቴክኖሎጂው በሚሰራጩ የሀሰት ወሬዎች፣ ብሄርን ወይም  ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ መረጃዎች ያለገደብ የሚለቀቅበት ሁኔታ አመዝኖ የስጋት ምንጭ  እየሆነ መጥቷል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ የሆነ ቡድን ወይም አካል መነሻው ምን እንደሆነ ለማወቅ በሚያዳግት መልኩ በስሜታዊነት የሚፈረጅበት፣ የጥላቻ መረጃዎች  እየተፈበረኩ በተቀናበሩ ፎቶዎች የሚቀርብበት፣ በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜያት ጸንተው ለነበሩ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን ለሚንዱ የጥላቻ መረጃዎች መጫዎቻ ሜዳ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ባሉ የሀሰትና የጥላቻ መረጃዎች በሀሪቱ ላይ እየፈጠሩ ባለው ችግርና መፍትሄው ላይ  ውይይት ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይም ሀገራችን ከማህበራዊ ሚዲያ ምን አተረፈች? በማለት በጥያቄ ሀሳባቸውን ማካፈል የጀምሩት በቀድሞው የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ  ቡድን መሪ  አቶ በቀለ እውነቱ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መረጃዎች ለህብረተሰቡ ከሚሰጡት ጠቀሜታ ይልቅ  ጉዳቱ እየበዛ  ነው ያሉት፡፡ ለመልካም ነገር የተጠቀሙ የአለም ሀገራት ፈለግ በመከተል ቢሰራበት በርካታ  ተግባራትን  በቀላሉ ለመከውንና አማራጭ  የመሆን  አቅም ያለው  ቴክኖሎጂ ነው ያሉት አቶ በቀለ "እኛም እያደረሰ ያለውን ጉዳት በመቀነስ እውቀት ለሚጨምሩና ኑሮን ለሚያቀሉ ተግባራት ማዋል ላይ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል’’ ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ሚዲያውን እየተጠቀመ ያለው ቢያንስ መጻፍና ማንበብ የሚችል የህብረተሰብ ክፍል ነው የሚሉት ባለሙያው መረጃን በመመልከትም ሆነ ሀሳቡን  ተቃውሞና ደግፎ የሚሳተፈው አካል ለበጎ ተግባር የመጠቀም ሂደት ገና አልዳበረም በማለትም  ትዝብታቸውን ገልጸዋል፡፡ በማህበራዊ ገጾች የሚተላለፉ መረጃዎችን የማመዛዘን አቅም ማዳበር ይጠይቃል  የሚሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አቢዮት ባዬ፤ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 17 ሚሊዮን ባላይ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡ ቀደም ሲል ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ባለመረጋገጡ ሰዎች በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብርና መብት እንዲከበር ማንነታቸውን በመደበቅ በስውር የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከፍተው ለዴሞክራሲ መጎልበት የሚሰሩበት ወቅት እንደነበር ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት። ከሞላ ጎደል ነገሮች በተስተካከሉበት በአሁኑ ወቅት ሀሳብን በነጻነት ለመግልጽ ምቹ በሆነት ዘመን በተቃራኒው ሀሰተኛ መረጃዎችን አቀናብሮ በማሰራጨት ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ፣ ብሄርን ከብሄር ወይም በሃይማኖቶች መካካል ቅራኔና ግጭት ለመፍጠር እየተሰራ ይታያል ይላሉ። ለሀገር ሰላምና አንድነትም ስጋት እየሆነ ይገኛል ነው ብለዋል፡፡ ሀሰተኛ ወሬዎችን እያጋነነ የሚያሰራጨው አካል ምን ፍላጎት ቢኖረው ነው? ለምን ይነግረኛል? ብሎ እራስን በመጠይቅና መረጃውን ከሌሎች ታማኝ ምንጮች በማጣራት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ነው ዶከትር አቢዮት  የገለጹት፡፡ የጥላቻ መረጃዎችን የሚለቁ አካላት አላማቸው ለበርካታ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች መልእከታቸውን መበተን በመሆኑ ሀሳቡን ደግፎ ወይም ተቃውሞ ምላሽ ባለመስጠት የድርጊቱ ፈጻሚዎችን አንድም እራሳቸውን ከሀሰት መረጃ እንዲያርሙ ወይም የተከታይነት ተጽኖ ማመናመን እንደሚገባም ባለሙያው መክረዋል፡፡ በሌላ ሰው ወይም ተቋም ስም ሀሰተኛ የማህበራዊ ገጽ በመክፈት የፈጠራ ወሬን ተዓማኒነት በሌላቸው ፎቶዎች በማቀናበር ሀገርንና ዜጎችን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃዎችን የሚያስተላልፉ አካላትን ለማስቆም እንደሀገር ቆም ብለን ማሰብ አያስፍልገንም? በማለት ሀሳባቸውን በጥያቄ ያነሱት የሀይማኖት አባት ሀጂተሸለ ኪሮ እንዳሉት ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን አንድነትና ሰላም አስጠብቆ ማስቀጠል አለበት ፡፡ “ማህበራዊ ሚዲያ በብሄሮችና በሃይማኖቶች መካካል የጥላቻ ወሬ መርጨት  ብቻ አይደለም” የሚሉት ሌላው  የሃይማኖት አባት አባ መላከሂወት ወልደየሱስ  በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ ጭምር የአሉባልታና የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት የመተማመንና የመከባበር  ባህልን እየሸረሸረ ነው ብለዋል፡፡ በርካታ የመረጃ አማራጮች መኖር መልካም አጋጣሚ መሆኑን የነገሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፤ መረጃዎች ሁሉ እውነተኛና ጠቃሚ ባለመሆናቸው ተፈትሸውና ተለይተው መወሰድ እዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ “በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ የሚቀርቡ መረጃዎች፤ የበሰለ የፖለቲካ ሀሰብን ከማቅረብ ይልቅ የአንድ ግለሰብን ወይም ቡድንን ስሜትና የጥላቻ መረጃ የሚቀርቡበት ሜዳ ሆኗል” የሚሉት ዶክተር ጌታቸው ህብረተሰቡ ስጋቱን እየተረዳው መምጣቱን ነው የተናገሩት። መደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሻሻሎችና አማራጭ የህዝብ የመረጃ ምንጭ እየሆነ ቢመጣም ለበርካታ አመታት “ለገዢው ሃይል  የሚዘምር” ነበር ይላሉ። ዶክተር ጌታቸው እንደሚሉት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለህብረተሰቡ የማስተማር፤ በቁጥር እያደገ በመጣው የኤፍ ኤምና ቴሌቭዥን መገናኛ ዘዴዎች መንግስት መረጃዎችን በፍጥነት መስጠትን በመፍትሄነት መጠቀም ግድ ይላል። ማንነቱን ያልገለጸ አካልን ጓደኛ ማድረግም ሆን መከትል እንደማያስፍልግም በማስረዳት፡፡ የድሬ ትዩብ መስራች እና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ነገሰ  ፌስ ቡክ የመጠቀሚያ ቴክኖሎጂውን በየጊዜው ይበልጥ ቀላልና ባለብዙ አማራጭ እያደረገው መምጣቱ በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን አደጋ ያባብሰዋል የሚል ስጋት ነው ብለዋል። አቶ ቢኒያም  "በድሬ ትዩብ ስም በተከፈት የሀሰተኛ  ገጽ ላይ በተለቀቀ የአንድ ድርጅት ስም ማጥፋት መረጃ እኛን ጥፋተኛ ሊያደርግ የነበረን ድርጊት የፌስቡክ ባለቤት ጋር በአካል በመሄድ ሀሰተኛ መሆኑን በማስረዳት የኛን ትክክለኛ ገጽ በማረጋገጥ ከችግሩ ዳን" በማለት በተሞክሮነት አንስተዋል፡፡ አሁን በሀገሪቱ  በማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ጥናት ላይ የተመሰረትና ቴክኖሎጂውን በአግባቡ በመጠቀም ብሎም ውጤት ካስመዘገቡ  ሀገራ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡ የጥላቻ ሀሳቦችን የሚያንጸባርቁ  ገጾችን የሚከላከል አንድ ተቋም በማቋቋምና በቂ እውቀት ያላቸው ባለሞያዎችን መድቦ መስራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ፌስቡክ በአፍሪካ ያለውን አገልግሎት የሚከታተልበት ቢሮ በደቡብ አፍሪካ  እንዳለው የገለጹት አቶ ቢኒያም፤ መንግስት ከተቋሙ ጋር በመነጋገር በሀሰተኛ ወይም በሌላ ተቋማትና ግለሰብ ስም አካውንት በመክፍት ሀገርን የሚጎዱ የጥላቻ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን የመቆጣጠርና ተጠያቂ የማድረግ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል በማለትም ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። እኛም ለዛሬ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ሥራ በመጠቀም የራሳቸውን ህይወት ጭምር ያሻሻሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችም አሉና ሁላችንም ለበጎ ተግባር በመጠቀም ለዜጎችም ሆነ ለሀገራችን ሥጋት ከመሆን የለውጥ ተስፋ እንዲንሆን የሁላችንም ጥረት ይጠይቃል እንላለን። ሠላም!  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም