ኢትዮጵያና ሴኔጋል የመጀመሪያ የሆነውን የጋራ የኮሚሽን ስብሰባ ሊያካሂዱ ነው

67
አዲስ አበባ ህዳር 9/2011 ኢትዮጵያና ሴኔጋል የመጀመሪያ የሆነውን የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ሊያካሂዱ ነው። አገራቱ የጋራ የኮሚሽን ስብሰባውን የሚያካሄዱት በመጪው ታህሳስ ወር 2011 ዓም አዲስ አበባ ውስጥ መሆኑም ተገልጿል። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ከሴኔጋል የአፍሪካ ጥምረት ሚኒስትር ምባኝክ ንዳዬ ጋር ዛሬ አዲስ አበባ  በተወያዩበት ወቅት ነው ይህ የተገለፀው። ውይይታቸው በዋናነት ሁለቱ አገራት በንግድ፣ በትምህርትና በስፖርት ዘርፎች በጋራ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው። የሴኔጋል የአፍሪካ ጥምረት ሚኒስትር ምባኝክ ንዳዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ። በጉኝታቸውም በአገራቱ የመጀመሪያው በሆነው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ይታደማሉ ብለዋል። የኮሚሽኑ ውይይት ትኩረትም የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ላይ እንደሚሆን ጨምሮ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መለሰ አለም በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሴኔጋል በአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ) ውሰጥ በጋራ ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። የሁለቱ አገራትን ጥቅሞች ማስጠበቅ በሚቻልበት መንገድ ላይ ተባብረው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ሚኒስትር ዴኤታዋ መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ አክለዋል። የጋራ ኮሚሽን ስብሰባው የተሳካ እንዲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚሰራም መናገራቸውን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያና ሴኔጋል ቆየት ያለ ግንኙነት ያላቸው አገራት ሲሆኑ በተለይ የቀድሞዎቹ መሪዎች ቀዳማዊ ኃይለስላሴና ሲደርስ ጉር ለአፍሪካ አንደነት መመስረት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም