የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ሳምንት ይጀመራል

71
አዲስ አበባ  ህዳር 8/2011 በስምንት ክለቦች መካከል የሚካሄደው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ህዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የውድድር ዓመቱ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም መከላከያ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል። ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም አዲስ አበባ ፖሊስ ከጣና ባህርዳርና ሙገር ሲሚንቶ ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሶዶ ላይ ወላይታ ዲቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ጋር ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። የሀበሻ ስሚንቶ የ2011 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉን ስፖንሰር በማድረግ ከኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ጠቁመዋል። የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለቮሊቦል እድገት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነና በወድድሩ ወቅት አልፎ አልፎ የሚታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ለመፍታት ፌዴሬሽኑ ትኩረት አድርጉ ይሰራል ብለዋል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከ2005 ዓ.ም በሁለቱም ጾታዎች የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸው የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በአሁኑ ሰአት ያሉትን አራት ክለቦች በመጨመር ውድድሩን ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።   ወላይታ ዲቻና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በቅደም ተከተል የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግና የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም