የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጎሉና በሚያጠናክሩ ተግባራት ይከበራል

58
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 በዘንድሮው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ብሔሮች የራሳቸውን ባህልና ትውፊት ከማጉላት ባሻገር የሌላውንም ይዘው የሚቀርቡበት እንደሚሆን ተገለጸ። በአዲስ አበባ በሚከበረው በዚሁ በ13ኛው በዓል ላይ 10ሺህ ያህል ሰዎችን የሚያሳትፉና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ተግባራትና የቡና መርሃ ግብርም እንደሚኖር ተገልጿል። በበዓሉ ላይ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የራሳቸውን ባህልና ትውፊት ከማስተዋወቅ ባሻገር የሌላውንም ይዘው የሚቀርቡበት እንደሚሆን ነው የ13ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ያስታወቀው። የፅህፈት ቤቱ ኃላፊና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነስረዲን መሐመድ በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት የሚከበረው የዘንድሮው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የአንድነት አስተሳሰብ በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ  እንደሚከበርም ተናግረዋል። በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱና የሚስተዋሉ አለመግባባቶች መነሻቸው "የአመለካከት ችግር ነው" ያሉት ኃላፊው ይህን የሚፈታ ሰነድም ተዘጋጅቶ ለውይይት እንደሚቀርብ አውስተዋል። በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚዘጋጀው በዚሁ ሰነድ ላይ የተለያዩ ኀብረተሰቦች እንደሚወያዩበትና ብዝሃነትን እንዲሁም ሰላምና መቻቻልን የሚያጠነክር እንደሚሆንም አስረድተዋል። ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሁነቶችን ያካተተው የዘንድሮው በዓል ብሄሮች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ይዘው የሚቀርቡበት መድረክ ይሆናል ነው ያሉት። በከተማ ደረጃ በስፋት በህፃናት የተጀመረ ስራ አለ ያሉት ኃላፊው በበዓሉ ላይ ከሁሉም ክልል የተውጣጡ 156 ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር ተሳታፊ በመሆን ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ ሌሎች ቢሮዎችንም እንደሚጎበኙ ገልጸዋል። በቀጣይም ወደ ክልላቸው ሲመለሱ በትምህርት ቤታቸውና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተጠቅመው ያገኙትን ልምድ ለሌሎች እንዲያጋሩ ስለሚደረግ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል ። በዘንድሮ በዓል ላይ 10 ሺ የኮሌጅና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ኃላፊው አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም